#FastMereja I በአሜሪካ የፓርኪንግ (የመኪና ማቆሚያ) አስተናጋጅነት እና ቁጥጥር ስራ የተሰማሩ ሰራተኞች በአማካይ በሰአት ከ15 እስከ 17 ዶላር ክፍያ እንደሚያገኙ የቅርብ ጊዜ የስራ ገበያ መረጃዎች አመላከቱ።
በአሜሪካ የኢንዱስትሪ መረጃዎችና የቅጥር ኤጀንሲዎች ይፋ ባደረጉት ትንተና መሰረት፣ በዚሁ ዘርፍ የተሰማሩ ሰራተኞች እንደ የስራ ቦታቸው፣ ልምዳቸው እና እንደሚሰሩበት ግዛት ሁኔታ በሰአት ከ9.62 ዶላር ጀምሮ እስከ 22.84 ዶላር የሚደርስ ገቢ ያገኛሉ። ይህም በዓመት በአማካይ ከ30,000 እስከ 36,000 ዶላር የሚደርስ አጠቃላይ ገቢ እንደሚያስገኝ ተመልክቷል።
በተለይም እንደ ካሊፎርኒያ፣ አላስካ እና ኮሎራዶ ባሉ ግዛቶች የፓርኪንግ ሰራተኞች ክፍያ ከተጠቀሰው አማካይ መጠን ከፍ ያለ ሲሆን፣ በሰአት እስከ 21 ዶላር የሚደርስ ክፍያ ይከፈላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም እንደ ቫሌት ፓርኪንግ ባሉ አሰራሮች ላይ የሚሰሩ ሰራተኞች ከተወሰነላቸው መሰረታዊ ደሞዝ በተጨማሪ ከአገልግሎት ተቀባዮች ከሚያገኙት ተጨማሪ ስጦታ (Tips) አጠቃላይ ገቢያቸውን ያሳድጋሉ።
የስራው ተፈጥሮ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎችን መቆጣጠር፣ ትኬት መስጠት፣ ደንበኞችን ማስተናገድ እና መኪና ማቆምን ማመቻቸት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ለስራው የሚጠየቀው መስፈርትም አነስተኛ መሆኑ ለብዙዎች የመጀመሪያ የስራ እድል እንዲሆን አድርጎታል።
