#FastMereja I ሀገርን፣ ህዝብን እና መልካም እሴቶችን በማስቀደድ በቲክቶክ፣ ፌስቡክ፣ ዩቲዩብ እና ቴሌግራም በጎ ተፅዕኖ ለፈጠሩ 36 የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በአጠቃላይ 15 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የ280 ግራም ወርቅ ሜዳሊያ እና ልዩ ልዩ ሽልማቶች የሚሰጥበት የዕውቅና መርሃ ግብር መዘጋጀቱ ተገለጸ።
ይኸው ግዙፍ የዕውቅና እና የሽልማት መርሃ ግብር ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ አላማ በሚያውሉ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች እና ህብረተሰብን የሚጠቅሙ አዳዲስ ሀሳቦች ባሏቸው ባለሙያዎች ላይ ያተኮረ ነው። መርሃ ግብሩ በሁለት ዋና ዋና ዘርፎች ተከፍሎ ሽልማቶቹን የሚያበረክት ሲሆን፣ ከመጀመሪያው ዘርፍ ከአመቱ ሙሉ የየወሩ አሸናፊዎች መካከል ለሚመረጡ ሶስት ተሸላሚዎች በአጠቃላይ 180 ግራም የወርቅ ሜዳሊያ ተዘጋጅቷል። በዚህም መሰረት አንደኛ ለወጣው ባለሙያ የ100 ግራም፣ ለሁለተኛው የ50 ግራም እንዲሁም ለሶስተኛው የ30 ግራም የወርቅ ሜዳሊያ የሚሰጥ ይሆናል።
በሁለተኛው ዘርፍ ደግሞ “ሀገር ተስፋ የምታደርጋቸው” በሚል መሪ ቃል በስራ ፈጠራ፣ በፋሽን ዲዛይን፣ በቱሪዝም፣ በካፒቴንነት፣ በትምህርት እና በተለያዩ ሙያዎች ተሰማርተው ህብረተሰቡ ዘንድ ብዙም ሳይታወቁ ለሀገር እና ለትውልድ የሚጠቅም ስራ ለሰሩ ሙህራን እና ባለሙያዎች የ100 ግራም ወርቅ ሜዳሊያ ሽልማት ተመድቧል። በዚህ ዘርፍ አንደኛ ለሚወጣው የ50 ግራም፣ ለሁለተኛው የ30 ግራም እና ለሶስተኛው የ20 ግራም የወርቅ ሜዳሊያ የሚበረከት ሲሆን፣ ከ4ኛ እስከ 20ኛ ደረጃ ለሚይዙ ተወዳዳሪዎችም ልዩ ልዩ የዕውቅና እና የስጦታ መርሃ ግብሮች ተዘጋጅተዋል።
በተጨማሪም ይኸው መርሃ ግብር የዘመኑን የዲጂታል መድረኮች ተጠቅመው ለሀገር ውለታ የዋሉ ከ10 በላይ የሀገር ባለውለታዎች የምስጋና ስነ-ስርዓት የሚያቀርብ ሲሆን፣ አጠቃላይ የሽልማት ዝግጅቱ የፈጠራ ሰዎችን ማበረታታት እና የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን ለሀገር ግንባታ ማዋልን አለማ ያደረገ መሆኑ ተጠቅሷል።
