banner

ደቡብ ሱዳን በዓባይ ወንዝ ላይ ግድቦችን ለመገንባት ሥጋት እንደሌላት ገለጸች

#FastMereja I የደቡብ ሱዳን የኢነርጂና ግድቦች ሚኒስትር አጎክ ማኩር ኩር ሀገራቸው በዓባይ ወንዝ (ተፋሰስ) ላይ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን ለመገንባት ምንም ዓይነት ሥጋት የሌላት መሆኑንና የልማት ፕሮጀክቶቿን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቁ። ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የታችኛው ተፋሰስ ሀገር የሆነችው ግብፅ “የውሃ ደህንነቴን ይነካል” በማለት በተፋሰሱ ሀገራት የሚከናወኑ የውሃ ልማቶችን እንደምትቃወም ባስታወቀችበት ወቅት ነው። ደቡብ ሱዳን የዓባይ ተፋሰስ አባልና ሉዓላዊት ሀገር በመሆኗ የተፈጥሮ ሀብቷን የማልማት ሙሉ መብት እንዳላት ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

​ሚኒስትር አጎክ ማኩር አክለውም የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ሚኒስትሮች ምክር ቤት ግብፅ በታደመችበት ስብሰባ ግድቦችን ጨምሮ 34 ፕሮጀክቶችን ማፅደቁን አስታውሰዋል። በመሆኑም ግብፅ እራሷ የተስማማችባቸው ፕሮጀክቶች በመሆናቸው ደቡብ ሱዳን የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን ለመገንባት የምትሰጋበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል። የመንግስታቸውን ዝግጅት አስመለክቶ ለፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ገለጻ ማድረጋቸውንና የውጭ ባለሀብቶች እንዲሁም አምባሳደሮች በፕሮጀክቶቹ ላይ ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቁመው፣ ዝርዝር መረጃዎች ወደፊት ይፋ እንደሚደረጉ ገልጸዋል።

​በሌላ በኩል፣ የፖለቲካና ዲፕሎማሲያዊ ተንታኙ ቦቦያ ጄምስ ለሬዲዮ ታማዙጅ በሰጡት አስተያየት፣ የደቡብ ሱዳን የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል የማልማት አቅም ከግብፅ ጋር በነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና በፖለቲካዊ ተጽዕኖዎች ምክንያት ሲስተናቀል መቆየቱን ገልጸዋል። ተንታኙ እንደ ሶኮሊ፣ ባደን እና ፉላ ያሉ በርካታ የግድብ ቦታዎችን በምሳሌነት የጠቀሱ ሲሆን፣ ደቡብ ሱዳን ከግብፅና ከሌሎች የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ጋር በጋራ መከባበር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት በመመስረት የኤሌክትሪክ አቅርቦቷን ማሳደግ እንዳለባት አሳስበዋል።

​የደቡብ ሱዳን መንግሥት የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት ፍላጎት ባቀናጀ መልኩ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የሀገሪቱን የኢንዱስትሪና የሥራ ዕድል ፈጠራ የማሳደግ እቅድ እንዳለው የራዲዮ ታማዙጅ እና የኤስኤስ24 ዘገባዎች ያመለክታሉ።

Leave a Comment