#FastMereja I የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መጠናቀቅን ተከትሎ መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም የመንግሥት ምሥረታ እና የምክር ቤቱ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡ አፈ-ጉባኤው በሰጡት መግለጫ፤ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ 10 ሺህ 438 ዕጩዎች እንዲሁም ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች የተሳተፉበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒነት ባለው ሁኔታ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑንና ተጠሪነቱም ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ ያስታወሱት አፈ-ጉባኤው፤ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመንም በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እንደሚጀምር በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 2 መደንገጉን አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 56 መሠረት በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጥምር ድርጅቶች የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል እንደሚያደራጅና እንደሚመራ ጠቅሰዋል፡፡
ለሥነ-ሥርዓቱ አስፈላጊው ዝግጅት ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን የጠቆሙት አፈ-ጉባኤው፤ በሕዝብ የተመረጠው አዲሱ መንግሥት ቀጣዩን አምስት ዓመታት ሀገርና ሕዝብ የመምራት ኃላፊነት እንደሚረከብ አረጋግጠዋል፡፡ በመጨረሻም መጪው ዘመን የሰላም፣ የጤና፣ የደስታ፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የብልፅግና እንዲሆን የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
