banner

የአፍሪካ ኅብረት በሰሜን ኢትዮጵያ ባጋጠመው ውጥረት አፋጣኝ ንግግር እንዲጀመር ጥሪ አቀረበ

#FastMereja I ​የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ የሱፍ በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎች ዳግም እያየለ በመጣው ውጥረት እና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጥልቅ ስጋታቸውን ገልጸዋል። ሊቀመንበሩ ይፋ ባደረጉት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የህወሓት ኃይሎች የመቀሌ፣ የአክሱምና የሽሬ አየር ማረፊያዎችን መቆጣጠራቸውን፣ የፌደራል አካላትን ማሰራቸውን እና የሲቪል አቪዬሽን አገልግሎቶችን ማስተጓጎላቸውን አውግዘዋል። በተጨማሪም በደቡብ ትግራይ እና በአፋር ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ እያየለ የመጣው ግጭት እንዲሁም አዳዲስ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ጥምረቶች መፈጠር ቀጠናውን የበለጠ እንዳያደፈርሰው ስጋት ፈጥሯል ተብሏል።

​ሊቀመንበሩ አክለውም በኖቬምበር 2022 እ.ኤ.አ በፕሪቶሪያ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተፈረመው ዘላቂ የተኩስ ማቆም ስምምነት ለሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ብቸኛው መሰረት መሆኑን ገልጸዋል። የሲቪል አየር ማረፊያዎችን በኃይል መቆጣጠር ከፕሪቶሪያው ስምምነት መርሆች ጋር የሚቃረን እና የተገኙትን የሰላም ፍሬዎች የሚያበላሽ በመሆኑ፣ ወገኖች ሁሉ ከማንኛውም ውጥረትን ከሚጨምሩ እንቅስቃሴዎች ታቅበው በስምምነቱ ማዕቀፍ ውስጥ አፋጣኝ የቀጥታ ውይይት እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርበዋል።

​በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት ውጥረቱን ከሚያባብሱ እርምጃዎች በመቆጠብ ለሰላምና ውይይት ድጋፍ እንዲያደርጉ የጠየቀ ሲሆን፤ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ኅብረት የቀድሞ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ አፋጣኝ የዲፕሎማሲ ጥረት በማድረግ ወገኖችን ወደ ውይይት እንዲመልሱ ጥሪ ማቅረባቸውን የአፍሪካ ኅብረት የመረጃና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ይፋ ያደረገው መግለጫ ያመለክታል።

Leave a Comment