#FastMereja I ከ20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ዋና የዕለታዊ ምግብ ምንጭ የሆነውና ድርቅን በመቋቋም የሚታወቀው እንሰት፣ በሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ሳይንቲስቶች ገልጸዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እያገኘ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በሀገር ውስጥ አርሶ አደሮች የገበያ ተፈላጊነታቸው ወደተሻሉ የንግድ ሰብሎች በመዞራቸው የእንሰት አመራረት እያቀነሰ መምጣቱን ሲኤንኤን (CNN) ዘግቧል።
እንደ ሲኤንኤን ዘገባ ከሆነ እንሰት የሚበላ ፍሬ አይሰጥም። ይልቁንም ኢትዮጵያውያን የግንዱን ታችኛ ክፍልና ከመሬት በታች ያለውን ሥሩን በመፋቅና በማቦካት ለቆጮ እና ለቡላ ዝግጅት ይጠቀሙበታል። ሰብሉ በደቡብና ደቡብ ምዕራብ ከፍተኛ ቦታዎች (ከባህር ጠለል በላይ ከ1,500 እስከ 3,000 ሜትር) የሚያድግ ሲሆን፣ 60 የእንሰት ተክሎች የአምስት አባላት ያሉት ቤተሰብ ለአንድ ዓመት መመገብ እንደሚችሉ ተመልክቷል።
በኪው የሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ የሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት ጄምስ ቦሬል እንደገለጹት፣ እንሰት እንደ ስንዴ፣ በቆሎና ሩዝ በየወቅቱ መዘራት የማያስፈልገው ዓመታትን የሚቆይ በመሆኑና ድርቅን እንዲሁም በሽታን የመቋቋም አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል። በፈረንሳይ እ.ኤ.አ. በ2021 የተደረገ ጥናት እንደሚያመላክተው፣ የእንሰት እርሻን በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት በ12 እጥፍ ማስፋፋት ከተቻለ ተጨማሪ 111.5 ሚሊዮን ሰዎችን ከምግብ እጥረት ማዳን ይቻላል።
ሆኖም ሰብሉ ከኢትዮጵያ ውጭ በስፋት እንዳይሰራጭ ባህላዊ፣ ህጋዊና ተግባራዊ እንቅፋቶች አሉበት። ኢትዮጵያ የባዮ-ፓይረሲ (የብዝሃ-ሕይወት ዘረፋ) ስጋትን ለመከላከል የዕፅዋት ዘሮችን ወደ ውጭ መላክ በጥብቅ የምትቆጣጠር ሲሆን፣ ከባድ የፊዚካል ድካም የሚጠይቀው የእንሰት ዝግጅት በዋናነት በሴቶች መከናወኑና ዘመናዊ ማሽኖች በስፋት አለመሰራጨታቸው ተግዳሮት ሆኗል። በተጨማሪም በ2025 ዓ.ም በኪው እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው፣ 60 በመቶ የሚሆኑ የደቡብ ምዕራብ አርሶ አደሮች የእንሰት መሬታቸውን ወደ ሌሎች የንግድ ሰብሎች መለወጣቸውን አረጋግጠዋል።





