banner

ዘምዘም ባንክ ያለ ተጨማሪ ክፍያ ገንዘብ የሚላክበትን “ዘምዘም ሪሚት” የተሰኘ አገልግሎት ይፋ አደረገ!

#Fastmereja:- በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመስጠት የሚታወቀው ዘምዘም ባንክ አ.ማ. “በማይነጥፍ ጽናት ወደ ላቀ ምዕራፍ!” በሚል መሪ ቃል 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እና የ”IFB Pioneers Forum” የምክክር መድረክን በዛሬዉ እለት በስካይላይት ሆቴል በደመቀ ሁኔታ አከበረ።

ባንኩ የ5ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሳይበር ደህንነት ምርመራ ያለፈውን እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ያገኘውን “ዘምዘም ሪሚት” (Zamzam Remit) የተሰኘ ዲጂታል የሐዋላ አፕሊኬሽን በይፋ ስራ አስጀምሯል።

አዲሱ አፕሊኬሽን በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የዲያስፖራ አባላት ያለ ተጨማሪ የአገልግሎት ክፍያ፣ ግልጽ በሆነ የምንዛሬ ተመን፣ በባዮሜትሪክ እና በPIN በተጠበቀ ደህንነት ገንዘብ ወደ ሀገር ቤት እንዲልኩ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም ወደ ሀገር ቤት በሚላክ እያንዳንዱ ሐዋላ ላይ ለተቀባዩ ተጨማሪ የገንዘብ ስጦታ (“ሂባ”) የሚያበረክት ልዩ ጥቅም ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ መሊካ በድሪ እንደገለጹት፤ ዘምዘም ባንክ ባለፉት አምስት ዓመታት የፋይናንስ ተደራሽነትን በማሳደግ እና የሸሪዓ መርሆችን የተከተለ ዘመናዊ አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ እመርታ አስመዝግቧል ሲሉ ተናግረዋል።

ከ”ዘምዘም ሪሚት” በተጨማሪ ባንኩ የሥራ ቅልጥፍናን የሚጨምሩ ስድስት አዳዲስ ዲጂታል ሥርዓቶችን ያስመረቀ ሲሆን፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የተደገፈው «አንሳር» ዲጂታል ፋይናንሲንግ አገልግሎት ያለ ንብረት ማስያዣ ለሴቶች፣ ወጣቶች እና አነስተኛ ነጋዴዎች ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ ፋይናንሲንግ ማቅረብ መቻሉ ተመላክቷል።

በአሁኑ ወቅት የዘምዘም ባንክ አጠቃላይ ሀብት ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ከ21 ቢሊዮን ብር እና የቀረበው የፋይናንስ አቅርቦት ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ መሻገሩ ተገልጿል።

የባንኩ ከታክስ በፊት ያለው ዓመታዊ ትርፍ 1.6 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ 5.6 ቢሊዮን ብር መድረሱ እንዲሁም የደንበኞቹ ቁጥር 1.1 ሚሊዮን ያለፈ ሲሆን የቅርንጫፎቹ ቁጥር 141፣ እንዲሁም የባለአክሲዮኖቹ ቁጥር ወደ 21 ሺህ ማደጉ ነዉ የተገለፀዉ።

በሌላ በኩል በ4,136 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፈው የባንኩ ዘመናዊ ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ዲዛይን ተጠናቆ የመሰረት ስራዎች መጀመራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ባንኩ ባስመዘገበው ላቀ አፈጻጸም በለንደን በተካሄደው Global Islamic Finance Awards (GIFA) መድረክ ለሶስተኛ ጊዜ የሻምፒዮንሺፕ ሽልማት አሸናፊ መሆኑ ተበስሯል።





Leave a Comment