banner

እስራኤል በሶማሊላንድ የመጀመሪያ አምባሳደሯን ሾመች

#FastMereja I እስራኤል ሉአላዊነቷን ለተቀበለችላት ለሶማሊላንድ የሾመችው የመጀመሪያው አምባሳደር ሚካኤል ሎቴም የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሙሐመድ አብዱላሂ (ሲሮ) አቀረቡ። በሀርጌሳ የፕሬዝዳንት ቤተመንግስት በተካሄደው የሹመት ደብዳቤ ማስረከብ ስነ-ስርዓት ወቅትም በሁለቱ ወገኖች መካከል ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ወይይት የተደረገ ሲሆን፣ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሀርጌሳ የኤምባሲ ህንፃ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ መርሃ ግብርም ተከናውኗል ሲል የዶቼ ቬለ (DW) የአፍሪካ ዘገባ አመልክቷል።

​ይህ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ እስራኤል ታህሳስ ወር 2018 ዓ.ም (ዲሴምበር 2025) ከሶማሊያ ተገንጥላ ራሷን ያወጀችውን ሶማሊላንድን በዓለም የመጀመሪያዋ ሀገር በመሆን በሉአላዊ ሀገርነት ከተቀበለች በኋላ የተደረገ ትልቅ ምዕራፍ ነው። በየካቲት ወር ላይም ሶማሊላንድ በእስራኤል የመጀመሪያ አምባሳደሯ አድርጋ መሾሟ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህም የሁለቱን ሀገራት ፈጣን የሁለትዮሽ እና የዲፕሎማሲ ትስስር ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።

​ሶማሊላንድ እ.ኤ.አ. በ1991 በሶማሊያ ከተከሰተው የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ከሞቃዲሾ መገንጠሏን ብታውጅም፣ የሶማሊያ ፌደራል መንግስት ግን ግዛቱ አሁንም የእኔ አካል ነው በማለት ይሞግታል። በእስራኤል እና በሶማሊላንድ መካከል እየተጠናከረ የመጣው ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በአፍሪካ ቀንድ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ አዳዲስ የፖለቲካ እና የጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶችን ማስከተሉ አልቀረም።

Leave a Comment