banner

ቪዥንፈንድ ማይክሮፋይናንስ ከጠቅላላ ተበዳሪዎች ውስጥ ሴቶች የ50 በመቶ ድርሻ መያዛቸው ተነገረ

#FastMereja I ቪዥንፈንድ ማይክሮፋይናንስ ተቋም አ.ማ. 8ኛ አስቸኳይ እና 27ኛ መደበኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤውን ህዳር 12 ቀን 2026 በሃይሌ ግራንድ ሆቴል አካሂዷል። ተቋሙ እ.ኤ.አ. ሰኔ 30 ቀን 2026 በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 2.8 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን የገለጸ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ43 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

በበጀት ዓመቱ የተቋሙ የተከፈለ ካፒታል 5.28 ቢሊዮን ብር፣ ጠቅላላ ካፒታሉ 7.38 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ጠቅላላ የሀብት መጠኑ 30 ቢሊዮን ብር መድረሱ በጉባኤው ላይ ተገልጿል። በተጨማሪም ለ145 ሺህ ተበዳሪዎች 21.1 ቢሊዮን ብር ብድር የተሰራጨ ሲሆን፣ በተበዳሪዎች እጅ የሚገኘው ጠቅላላ ተሰብሳቢ ብድር በ65.9 በመቶ አድጎ 23.05 ቢሊዮን ብር ሆኗል። የተቋሙ የቁጠባ መጠንም የ41 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል።

በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 121 ቅርንጫፎቹ ከ2 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማገልገል ላይ የሚገኘው ቪዥንፈንድ፣ ከጠቅላላ ተበዳሪዎቹ መካከል 57 በመቶዎቹ በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ እንዲሁም በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ መሆናቸውን አስታውቋል። ከጠቅላላ ተበዳሪዎች ውስጥ ሴቶች የ50 በመቶ ድርሻ መያዛቸውም ተመላክቷል።

በዲጂታል ፋይናንስ ዘርፍም ተቋሙ በ«ቪዥን መሪ» ዲጂታል አነስተኛ ብድር፣ በቴሌብር፣ በETH QR እና በዲጂታል እቁብ አገልግሎቶች ተደራሽነቱን አስፋፍቷል። በዓመቱ በሞባይል ባንኪንግ ብቻ 882 ሺህ 988 ግብይቶች ተከናውነው 5.81 ቢሊዮን ብር መንቀሳቀሱ ተገልጿል።

ተቋሙ በተያዘው የሂሳብ ዓመት የተበዳሪዎችን ቁጥር፣ የብድር አቅርቦትን፣ ቁጠባ ማሰባሰብን እንዲሁም የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቱን ጥራትና ተደራሽነት ይበልጥ ለማሳደግ አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።





Leave a Comment