…
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የክልሉ የአስተዳደር እና የጸጥታ አካላት የመከላከያ ሰራዊት አባል ለመሆን የሚፈልጉ ዜጎችን ምልመላ እናከናውናለን በሚል የሰራዊቱን አሠራር እና መስፈርቶች በጣሰ ሁኔታ ሕፃናትን ጨምሮ ሰዎችን በግዳጅ ስለመያዛቸው እና የተያዙትን ለመልቀቅ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲከፍሉ ስለማስገደዳቸው የደረሱትን መረጃዎች ተከትሎ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከኅዳር 4 እስከ 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ክትትል እና ምርመራ አከናውኗል።
ኢሰመኮ በዚህ ክትትል እና ምርመራ በኦሮሚያ ክልል፣ በአዳማ፣ በቢሾፍቱ፣ በጅማ እና በሻሸመኔ ከተሞች የሚገኙ እጩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ማቆያ ስፍራዎችን በመጎብኘት፤ በማቆያ ስፍራዎቹ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን በማነጋገር፤ እንዲሁም የሚሊሻ እና የፖሊስ ተቋማትን ጨምሮ ከክልል እስከ ቀበሌ መዋቅር ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን በማወያየት ስለጉዳዩ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን አሰባስቧል።
ኢሰመኮ በሻሸመኔ ከተማ ባደረገው ክትትል እና ምርመራ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች መሆኑን የገለጹ ሕፃናት “ወታደራዊ ስልጠና ትገባላችሁ” በሚል ወደ ማቆያ አዳራሾች እንዲገቡ መደረጋቸውን አረጋግጧል። በሁሩፋ ክፍለ ከተማ፣ ሀሌሉ ወረዳ ውስጥ በማቆያ አዳራሽ ከነበሩ እና ኢሰመኮ ካነጋገራቸው 32 ሰዎች መካከል 14ቱ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 16 ዓመት መሆኑን የገለጹ ሲሆን አንድ ሕፃን ደግሞ ዕድሜው 11 ዓመት መሆኑን ገልጿል። ከትምህርት ቤት ሲወጡ ከነዩኒፎርማቸው ሀሌሉ ወረዳ ወደ ሚገኘው ማቆያ አዳራሽ እንዲገቡ የተደረጉ የ5ኛ ክፍል ተማሪ የሆኑ ሁለት የ15 ዓመት ሕፃናት ወደ አዳራሽ ከገቡ ሁለት ሳምንት እንደሆናቸው ገልጸው የገቡበትን ሁኔታ ሲያስረዱ፦
“ከትምህርት ቤት ስንመለስ መከላከያ ለሚገቡ 25,000 ብር ይሰጣል ብሎ አንድ ግለሰብ በባጃጅ አሳፈረን፤ ከዚያ 010 ቀበሌ (ሀሌሉ ወረዳ) ወደ ሚገኘው አዳራሽ ገባን፤ ነገር ግን ከገባን በኋላ መውጣት አልቻልንም” ሲሉ ለኢሰመኮ ገልጸዋል፡፡
በጅማ ከተማ ኢሰመኮ ያነጋገረው የ14 ዓመት ሕፃን ስለተያዘበት ሁኔታ ሲያስረዳ፦
“ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡30 ሰዓት አካባቢ ወደ ቤት እየሄድኩ እያለሁ መንገድ ላይ ቆመው የነበሩ ሚሊሻዎች ባትሪ አብርተውብኝ አስቆሙኝ፤ መታወቂያ ሲጠይቁኝ ዕድሜዬ ገና 14 ዓመት ነው፤ የ7ኛ ክፍል ተማሪ ነኝ መታወቂያ የለኝም ብዬ ስመልስ፣ ቀበሌ ሄደህ ጉዳይህ ይጣራል በማለት ወደ ቀበሌ ወስደው ብዛታቸው ከ20 በላይ ከሚሆኑ ወጣቶች መካከል ቀላቅለውኝ ሄዱ። ለመከላከያ ሰራዊት አባልነት መያዜንም ወጣቶቹ ናቸው የነገሩኝ። በማግስቱ በድብቅ ለቤተሰቦቼ ደውዬ ካሳወቅኩ በኋላ ለመውጣት ችያለሁ” ብሏል።
በግዳጅ የተያዙ ሰዎች
በሻሸመኔ ከተማ ሁሩፋ ክፍለ ከተማ ሀሌሉ ወረዳ (010 ቀበሌ) ማቆያ አዳራሽ ውስጥ ከነበሩ እና ኢሰመኮ ካነጋገራቸው 32 ሰዎች መካከል፣ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ 13 ሰዎች ያለ ፈቃዳቸው በፖሊስ እና በሚሊሻ አባላት ተይዘው እንደገቡ፤ በአዳራሹ ከሳምንት በላይ እንደቆዩ እና መውጣት እንዳልቻሉ ገልጸዋል። በማቆያው ውስጥ የነበረ 1 ሰው ስለተያዘበት ሁኔታ ለኢሰመኮ ሲያስረዳ፣ በምሽት ወደ ቤቱ እየሄደ ሳለ ሚሊሻዎች ይዘውት ወደ አዳራሽ እንዳስገቡት እና ከተያዘ 4 ቀናት እንደሆነው አስረድቷል። ሌላ ለኢሰመኮ ምስክርነቱን የሰጠ ሰው ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ ለልጁ እራት ለመግዛት ከቤት ሲወጣ ያለምንም ምክንያት በሚሊሻ ተይዞ ወደ አዳራሹ እንደገባ ገልጿል።
በዚሁ በሀሌሉ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው አዳራሽ ተይዘው ከነበሩ እና ኢሰመኮ ካነጋገራቸው ሰዎች መካከል ዕድሜው 45 ዓመት እንደሆነ እና 4 ልጆችን ያለ እናት እንደሚያሳድግ የገለጸ አንድ ግለሰብ፣ ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት አካባቢ ከቤቱ ሲወጣ እንደተያዘ ገልጿል።
በተመሳሳይ በሁሩፋ ክፍለ ከተማ ቡልቻና ወረዳ ውስጥ በሚገኝ አዳራሽ ተይዘው ከነበሩ እና ኢሰመኮ ካነጋገራቸው 22 ሰዎች መካከል 4 ሰዎች፣ እንዲሁም በአለቼ ክፍለ ከተማ በአዋሻ ወረዳ ኢሰመኮ ካነጋገራቸው 10 ሰዎች መካከል 2 ሰዎች ከምሽቱ 2፡00 እስከ 3፡00 ሰዓት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ከሥራ ሲመለሱ በሚሊሻ እና በፖሊስ አባላት ተይዘው ያለፈቃዳቸው ወደ ማቆያ አዳራሽ እንደገቡ ገልጸዋል፡፡ ኢሰመኮ በጎበኛቸው የማቆያ አዳራሾች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በተመሳሳይ መንገድ በተለይ በምሽት በርካታ ሰዎች ከፈቃዳቸው ውጪ በሚሊሻ እና በፖሊስ ተይዘው ወደ ማቆያ አዳራሾቹ እንደገቡ ገልጸዋል። በተጨማሪም ኢሰመኮ በቡልቻና ወረዳ አንድ የአእምሮ ሕመም ያለበት ሰው በሚሊሻ አባላት በግዳጅ ወደ ማቆያ አዳራሹ እንዲገባ መደረጉን ከቤተሰቡ እና ከግለሰቡ ጋር ከነበረው ውይይት ለመገንዘብ ችሏል።
ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ዱከም ክፍለ ከተማ ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን አካባቢ ለዕለት ሥራ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሁለት ወጣቶች “ለመከላከያ ሰራዊት አባልነት ትመለመላላችሁ” በሚል ከሌሎች 15 ከሚሆኑ ወጣቶች ጋር በኦሮሚያ ፖሊስ አባላት እንደተያዙ እና ለሁለት ቀናት ከታሰሩ በኋላ በቤታሰቦቻቸው እና በዘመዶቻቸው ጥረት በተደረገው ድርድር መለቀቃቸውን አስረድተዋል፡፡
የተያዙ ሰዎችን ለመልቀቅ ገንዘብ እንዲከፍሉ ስለማስገደድ
አንዳንድ የክልሉ ሚሊሻ አባላት ወጣቶችን ለመከላከያ ሰራዊት አባልነት ምልመላ በሚል ከያዙ በኋላ ለመልቀቅ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲከፍሉ ያስገደዱ መሆኑን ኢሰመኮ አረጋግጧል። ይህ ገንዘብ እንዲከፈል የማስገደድ ድርጊት በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ሪፖርት የተደረገ ሲሆን በተለይም በአዳማ ከተማ እና አካባቢው ተስፋፍቶ ሲፈጸም የነበረ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
በአዳማ ከተማ በአንጋቱ ወረዳ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት አካባቢ ዳቦ ለመግዛት ከቤት የወጣ የ15 ዓመት ሕፃን እና የ8ኛ ክፍል ተማሪ በወረዳው ሚሊሻዎች ተይዞ ጨፌ ቀበሌ ፊት ለፊት በሚገኝ የእህል መጋዘን ውስጥ ተይዞ እንደነበር የገለጸች ኢሰመኮ ያነጋገራት እናት ምግብና ልብስ መውሰድ እንደማይፈቀድና በሚሊሻ እንደሚቀርብለት እንደነገሯት፤ በመጋዘኑ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ወጣቶች በተመሳሳይ ሁኔታ ተይዘው እንደነበሩ እና የአብዛኞቹ ቤተሰቦች ከ20,000 እስከ 100,000 ብር መጠየቃቸውን መስማቷን ገልጻለች። በዚሁ ጨፌ ቀበሌ ፊት ለፊት በሚገኘው መጋዘን ተይዞ የነበረ ሌላ የ15 ዓመት ሕፃን ወላጆች 20,000 ብር ካልከፈሉ ልጃቸው “ለወታደራዊ ስልጠና” እንደሚላክ የተነገራቸው መሆኑን ለኢሰመኮ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ 1 መረጃ ሰጪ ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት 12፡00 ሰዓት አካባቢ “ውትድርና ስልጠና ይሄዳል” በሚል 6 በሚሆኑ የሚሊሻ አባላት የተያዘ የ25 ዓመት ወንድሙን ለማስለቀቅ 30,000 ብር እንዲከፍል መጠየቁን እና ኢሰመኮ ባነጋገረው ወቅት ገንዘቡን በማፈላለግ ላይ እንደነበር አስረድቷል። ወንድሙ በተያዘበት ስፍራ ሌሎች በርካታ ሰዎች ተይዘው እንደነበረ እና ዐቅማቸው የሚፈቅድ የተያዙ ሰዎች ቤተሰቦች ከ20,000 እስከ 30,000 ብር እየከፈሉ ያስለቀቁ መሆኑን ገልጿል።
ጥቅምት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት አካባቢ በአዳማ ከተማ ደካ አዲ ወረዳ ነዋሪ የሆነ አንድ የ21 ዓመት ወጣት ከሥራ ወደ መኖሪያ ቤት በመመለስ ላይ እያለ ተይዞ በወረዳው አስተዳደር አዳራሽ ለ4 ቀናት እንዲቆይ ተደርጓል። የወረዳው ሚሊሻ አባላት ወላጅ እናቱን 25,000 ብር ካልከፈለች “ለውትድርና ስልጠና” ወደ ሌላ ቦታ እንደሚልኩት በማስፈራራት ገንዘቡን ከተቀበሉ በኋላ ወጣቱን መልቀቃቸው ተገልጿል።
ኅዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡00 ሰዓት አካባቢ በአዳማ ከተማ ጨፌ ቀበሌ 1 በቀን ሥራ የሚተዳደር የ16 ዓመት ሕፃን በቀበሌው ሚሊሻ አባላት በቁጥጥር ሥር ውሎ ቤተሰቦቹ 30,000 ብር እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን እና ዐቅም የሌላቸው መሆኑን ከገለጹ በኋላ ወደ ቀበሌው አስተዳደር እንዳይመለሱ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው፤ ሕፃኑም መረጃው ለኢሰመኮ እስከደረሰበት ኅዳር 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ተይዞ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።
