አይኤፍኤች ኢንጂነሪንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር/ 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አስመልክቶ ያዘጋጀው የ10ኪሎ ሜትር ሩጫ የተለያዩ የመንግስት አካላትና አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ በተገኙበት በነገው እለት እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ከሃምሳ በላይ ፕሮጀክቶችን ሰርቶ ያስረከበው አይኤፍኤች ኢንጂነሪንግ ላለፉት 18 ዓመታት ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን (AACRAJ) እና ታላቁ ሩጫ ጋር በመተባበር ዓመታዊ የ10ኪሎ ሜትር ሩጫ በማስተባበር የቻይና እና ኢትዮጵያ ወዳጅነት እና ትብብርን በማጠናከር ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የዘንድሮው የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ የኩባንያውን 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እና ስኬትን ለማክበር ያለመ ሲሆን ሩጫውም የሚካሄደው ኩባንያው በቅርቡ አጠናቅቆ በሚያስረክበው ከቃሊቲ እስከ ቱሉ ዲምቱ ባለው መንገድ ላይ እንደሆነ ተገልጾ በዚህም ዝግጅት ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ታዋቂ እንግዶች እንደሚገኙበት ተነግሯል።
አይኤፍኤች ኢንጂነሪንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር/ የቀድሞ ስሙ ሲአርቢሲ አክሊስ ኢንጂነሪንግ ፕሌ፣ በኢትዮጵያ የተቋቋመ ታዋቂ የሲራዴ 1 ተቋራጭ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ የመንገድና የድልድይ ግንባታ እንዲሁም የኤርፖርት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ ግዙፍ ተቋም ነው።




