በጅማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በቡናና ሻይ ቅጠል ምርት ከ 2.6 ቢሊዮን ብር በላይ ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ስራ ሊጀምሩ ነው።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) እና የጅማ ዞን ዋና አስተዳደር ቲጃኒ ናስር በጂማ ዞን ማና ወረዳ በክላስተር እየለሙ ያሉ የቡናና ሻይ እርሻዎችን ፤ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎችን ተመልክተዋል።
ዶ/ር ፍሰሃ በጉብኝቱ ከአርሶአደሩ ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር ቡናን ፕሮሰስ በማድረግ ሙሉ በሙሉ ለዉጭ ገበያ የሚያቀርቡና ከ2.6 ቢሊዮን ብር በላይ ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ለመግባት በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልፀው ይህም በግብርና ምርት ላይ እሴት በመጨመር የምናጣውን ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሪ ከማስቀረቱም በላይ በጅማና አካባቢዋ ለሚገኘዉ አርሶአደር ዘላቂ የገበያ ትስስር የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል ።
የኩባንያዎቹ ወደ ስራ መግባት በጂማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት መነቃቃት የሚጨምርና በአካባቢው ላይ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት መሰረት ያደረጉ ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶች ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያበረታታ መሆኑን ዶ/ር ፍሰሃ በጉብኝቱ ወቅት ገልፀዋል ።
የዞኑ ዋና አስተዳደር አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው የጅማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በቡናና ሻይ ልማት ለተሰማሩ የአካባቢው አርሶአደሮች ትልቅ ፀጋ ነዉ ያሉ ሲሆን በልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ከአቮካዶ ፍሬ ዘይት በማምረት ለአሜሪካ ገበያ የሚያቀርበው አክሻይ ጄ ለዚህ ማሳያ ነዉ ያሉ ሲሆን ፤ ካምፓኒው ከ 10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአቮካዶ ምርት አቅራቢ ገበሬዎች ዘላቂ የገበያ ትስስር መፍጠሩን ለአብነት ያነሱ ሲሆን ይህንን መልካም አጋጣሚ ወደ ቡናና ሻይ ምርትም ለመቀየር በኮርፖሬሽኑ በኩል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን አንስተው ፤ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም ገልፀዋል ።
ቡናና ሻይ ቅጠልን በማቀነባበር ሙሉ በሙሉ ለዉጭ ገበያ የሚያቀርቡት ኩባንያዎቹ ወደ ስራ ሲገቡ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ያለውን የዉጭ ምንዛሬ ግኝትና የኤክስፖርት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ከማሳደጋቸው በተጨማሪ ከ 2ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶች ዘላቂ የስራ ዕድል ይፈጥራሉ።



