የሲዳማ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በሎካ አባያ ወረዳ እና አበላ አባያ ወረዳ ድንብር ላይ የተፈጠረውን ግጭት በዘለቄታዊነት ለመፍታት እየተወሰደ ያለውን እርምጃ አድንቀዋል።
ከሰሞኑ በሎካ አባያ ወረዳ እና በአበላ አባያ ወረዳ ድንበር ላይ በተነሳው ግጭት ጉዳቶች መድረሳቸውን ይታወቃል።
የሲዳማ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት አቶ አብርሃም ማርሻሎ በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ክስተት እንዳሳዘናቸው ገልፀው። በአከባቢው የተፈጠረው ክስተት ድጋሚ እንዳይከሰት በሁለቱም ክልል የፀጥታ አካላት፤ በሀይማኖት አባቶች፤ በሽማግሌዎች፤ በሁለቱም ወረዳ አስተዳዳሪዎች በኩል እየተደረገ ያለው ብርቱ እንቅስቃሴ የሚደነቅ መሆኑን ገልፀዋል።
አቶ አብርሃም ቀጠይነትም በሁለቱም ህዝቦች መካከል ያለው ወንድማማችነት መስተጋብር በውስን አጀንዳ ፈጣሪዎች እንዳይሸረሸር የጋራ መድረክ በመፍጠር ንግግሮች በማድረግ እና ችግሮችን ዘለቂታዊ መፍትሄ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
አቶ አብርሃም ማርሻሎ ሰላም የጋራ ሀብታችን ብቻ ሳይሆን የሁለንተናዊ ብልፅግና ጽኑ መሰረት ነው ያሉ ሲሆን “ሰላም ህዝቦች በአንድነት አብረው የሚያፈሩት ፣ የሁለንተናዊ ብልፅግና ጽኑ መሰረት ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ሰላም መተማመናችን ነው፤ ሰላም የሁላችንም የአብሮነት ጉዞ ነው፤ ሰላም አለመግባባትና ተቃርኖዎችን በሰለጠነ መንገድ መፍታት የሚያስችል መንገድና ግባችን መሆናቸውንም አሳውቀዋል።
ሰላም በእያንዳንዳችን እጅ እና ልቦና ውስጥ የሚገኝ ውድ ሀብት ነው። በመሆኑም ሌት ተቀን እንደ ዓይናችን ብሌን ልንከባከበው የሚገባ ፣ አንዳችን ለአንዳችን የሰላም ምንጭ እንጂ የስቃይ ምንጭ እንዳንሆን ከቆረጥንና ለተግባራዊነቱ ከተጋን ሰላም በደጃችን፣ በእጃችን ያለ ሀብት ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።
የሁለትም ህዝቦች ታሪካዊ ዳራ እንዲሁ ዝም ብሎ በአለመግባባት እና በውስን ግጭት ፈጣሪዎች የሚጠፋ አለመሆኑንም የሲዳማ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ አሳውቀዋል።
ለሀገራችን የሁሉ ነገር መሰረት የሆነው ብቸኛ መፍትሄና አማራጭ ሰላምን ማስፈን ነው ፤ አሁንም ይሁን ለቀጣይ ለሀገራችን ፍቱን መድሃኒት የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ የተረጋገጠበት ዘላቄታዊ ሰላምን እውን ማድረግ ስለሆነ በቀጣይም ዘላቂ ሰላም እንዲፀና ሁላችንም ስለ ሰላም የበኩላችንን እንድንወጣ እና አዎንታዊ አሻራ እንድናሳረፍ ጥሪ አስተላልፈዋል።