#FastMereja I አዋሽ ባንክ ስራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታትና ተገቢውን የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ሲያካሂድ የነበረውን የ2ተኛው ምዕራፍ የ”ታታሪዎቹ” የስራ ፈጠራ ውድድር የማጠቃለያ መርኃ-ግብር ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የባንኩ የስራ ኃላፊዎችና የተወዳዳሪ ቤተሰቦች በተገኙበት ዛሬ ጥር 20 ቀን 2017 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል የመዝጊያ ስነ ሥርዓት ተካሂዷል።
የአዋሽ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፀሀይ ሽፈራው በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት አዋሽ ባንክ ላለፉት 30 ዓመታት ለአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት እና ለሕብረተሰባችን የኑሮ መሻሻል አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን እና ባንኩ የአነስተኛና ጥቃቅን ቢዝነሶች የወደፊቷን ኢትዮጵያ ማሳደግ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው መሆኑን በመረዳት ባንኩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአንደኛው ምዕራፍ የስራ ፈጠራ ውድድር አሽናፊዎች ባንኩ በገባው ቃል መሰረት አሸናፊዎቹ የተመቻቸላቸውን ከዋስትና ነፃ የሆነ ብድር በመጠቀም በአሁን ወቅት ፕሮጀክታቸውን ወደ ተግባር በመቀየር አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ እንደሚገኙ እና ለዚህም ባንኩ የግንኙነት ስራ አስኪያጆችን መድቦ ተገቢው ክትትልና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ በሁለተኛው ምዕራፍ የስራ ፈጠራ ውድድር ላይ አዳዲስ እና ችግር ፈቺ የሆኑ የስራ ሀሳብ ያላቸው ከሁሉም የአገራችን ማዕዘን የተወጣጡ 5000 የሚጠጉ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉበት ሲሆን ከተመዘገቡት ተወዳዳሪዎች መካከል ከ1,688 በላይ የሚሆኑት ስራ ፈጣሪዎች ተለይተው በሁሉም ክልሎች በሰላሳ የስልጠና ማዕከላት እና በሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች በአስር ቋንቋዎች የክህሎት ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉ ተነግሯል።
በውድድሩ ከፍተኛ ውጤት ያገኙ አምስት ተወዳዳሪዎች እንደየ ደረጃቸው ከብር 200 ሺህ እስከ ብር አንድ ሚሊዮን የተሸለሙ ሲሆን ከዋስትና ነፃ እስከ ብር 5 ሚሊዮን ብድር እንደየ ፕሮጀክታቸው ሁኔታ ይመቻችላቸዋል ተብሏል። በሌላ መልኩ በዚህ ውድድር ከ6ኛ እስከ 12ኛ ለወጡ ተወዳዳሪዎችም ከ40 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ውድድሩን ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ያጠናቀቁት
1ኛ ሲሳይ ወልደገብርኤል (1 ሚሊዮን ብር)
2ኛ ዲቦራ ስንታየሁ (700ሺህ ብር)
3ኛ ቴዎድሮስ ገበየሁ (500ሺ ብር)
4ኛ ሜሮን ተስፋዬ (200ሺ ብር)
5ኛ ቤዛዬ አበራ (200ሺ ብር)
በመጨረሻም ባንኩ ይህንን የታታሪዎች የስራ ፈጠራ ውድድርን የማህበራዊ ኃላፊነት አካሉ አድርጎ እንደ አንድ ትልቅ ብራንድ ይዞ የሚቀጠል መሆኑን እና በሚቀጥለው ዓመት የሚሰጠው የገንዘብ ሽልማት እና የብድር መጠን ጥናት በማድረግ የሚሻሻል መሆኑን ተገልጿል።




