banner

የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ልዑካን ቡድን ኢትዮ ኢስታንቡል ሆስፒታልን ጎበኙ

#FastMereja I ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቴዎስ ሣልሳዊ የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ መልዕክተኛ የልዑካን ቡድን ሜትሮ ፖሊታን ማር ዩልዮስና ፋዘር ጆሲ ጃኮብ የኢትዮ-ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታልን ዛሬ ጥር 22/2017 ዓ.ም ጎበኙ።

አቶ ብርሃን ተድላ ኢትዮ-ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈፃሚ በጉብኝቱ መርሐግብር ወቅት ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ከሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር መቀራረቡ በተለይ ከፍተኛ ሕክምናዎችን በሀገር ውስጥ ለማድረግ ሆስፒታሉ ያለውን ራዕይ ለማሳካት የሚረዳ ነው።

ሆስፒታሉ በቴክኖሎጂ በታገዙ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችና ከፍተኛ ልምድ ባካበቱ ስፔሻሊስትና ሰብ-ስፔሻሊስት ባለሙያዎች በመታገዝ ዜጎቻችንን ለህክምና ወደ ውጭ አገር በመሄድ የሚያወጡትን ከፍተኛ ወጪና እንግልት ለማስቀረት እና ውጭ አገር የሚያስኬዱ ሕክምናዎችን በሀገር ውስጥ ለመስጠት አላማው አድርጎ የተነሳ በዋናነት በአዋቂና በህፃናት የልብ ቀዶ ህክምና ላይ የተሰማራ የሕክምና ተቋም ስለመኾኑ አብራርተዋል። በተጨማሪ የደረትና የሳንባ ቀዶ ጥገና ሕክምና፥ የጭንቅላትና ህብለሰረሰር ህክምና፥ የነርቭ ህክምና፥ የኩላሊት እጥበትና ህክምና፥ የአጥንት ቀዶ ሕክምና እና ጠቅላላ ህክምና ከመስጠቱ ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለልብ ሕሙማን ህፃናት ያለ ክፍያ የቀዶ ህክምና በመስጠት የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ብርሃን ገልፀዋል።

በዚህም እስከአሁን ድረስ ከ60 በላይ ለሆኑ የልብ ህሙማን ሕፃናትና አዋቂ ያለክፍያ እና በእገዛ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

የሕንድ ኦርቶዶክስ የፓትያርኩ ተወካይ በጉብኝቱ ወቅት ባዩት ኹሉ መደሰታቸውን ገልፀው በትብብር መሥራት የእነሱም ፍላጎት መሆኑን ተናግረዋል።

ህንድ አራት ሆስፒታሎች ላይ በቦርድ አባልነት እና ሊቀመንበርነት እንደሚያገለግሉ ገልፀው ኢትዮ ኢስታንቡል ሆስፒታል ከእነዚህ ተቋማት ጋር አብሮ እንዲሰራ ፣እዚህ የማይሰጡ ህክምናዎችን እሳቸው ከሚያስተባብራቿው ሆስፒታሎች ጋር አብሮ እንዲሰራ እና ድጋፍ እንዲያገኝ የበኩሌን አስተዎፇ አደርጋለሁ ብለዋል።





1 comment

El Roi January 30, 2025 - 1:54 pm

ከሃገራችን ውጪ ያሉ ኦርቶዶክሶች ታቦት የላቸውም ለምንድነው ታቦት የሌላቸው?

Reply

Leave a Comment