#FastMereja I የኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማህበር ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ጋር በመሆን እሁድ የካቲት 16/06/2017 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ የመክፈቻ ስነሥርዓት አካሄደዋል።
በዚህ በኮንፈረንስ ላይ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር የተከበሩ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ እንቁ ፓን አፍሪካኒስት ፕሮፌሰር ሉሙምባ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለ ስልጣናት፣ ሚንስትሮች፣ ሚንስትር ድኤታዎች፣ እንዲሁም የተለያዩ የአፍሪካ ወጣት መሪዎች፣ የኤምባሲ አምባሳደሮች፣ የዩኤን ኤጀንሲዎች፣ የተለያዩ አለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተገኝተውበታል።
በኮንፈረንሱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የምንመኛትን የበለፀገችና አንድነቷ የተረጋገጠ አፍሪካ እውን ለማድረግ ወጣቶች እምቅ አቅማቸውን ሊጠቀሙና በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ሐይለማሪያም ደሳለኝን በበኩላቸው ያለሰላም ጠንካሪ ኢኮኖሚን መገንባት፣ ፈጠራንና ዘላቂ ዕድገትን ማረጋገጥ አዳጋች መሆኑን ገልፀው ወጣቶች ችግሮችን በውይይት የመፍታት ልምድ ሊያዳብሩ እና በሰላም ግንባታ ሂደት ወሳኝ ሚናቸውን ሊጫወቱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኮንፈረንሱ ስለአመራርነት፣ ስለዲፕሎማሲ እና ስለ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት፣ ስለፈጠራ ሰፊ ውይይት ለማካሄድ ያለመ እንደሆነ የኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማህበር ዳይሬክተር ወጣት ኢንጂነር ጫላ አሰፋ ገልጿል። ኮንፈረንሱ ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በመድረኩ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት፣ ዩኒቨርስቲዎችና ከሲቪክ ማህበራት የተውጣጡ ከ300 በላይ ወጣት መሪዎች እየተሳተፉ ይገኛል።




