#FastMereja I ማዕዶት የኪነጥበብ እና መንፈሳዊ ኩነቶች አዘጋጅ የሚያዘጋጀው ማዕዶት ለኢትዮጵያ የተሰኘው ኦርቶዶክሳዊ የኪነጥበብ መርሐግብር እሑድ ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚከውን ዛሬ በስቱዲዮው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቋል።
12ኛ ዙር የሞላው ይህ መርሐግብር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በጣርማበር ወረዳ በአርማንያ ቀበሌ በስተደቡብ ጋሹ አምባ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ ለሚገኘው ቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተክርስቲያን ሕንጻ ማስፈጸሚያ እንደሚውል በመግለጫው ላይ የተገለጠ ሲሆን፤ ደብሩ የዛሬ 307 ዓመታት በ1710 ዓ.ም ከሸዋ አሥራ ሦስቱ ባላባቶች አንዱ በሆኑት ከመንዝ ግሼ አውሳቢ ልጅ በሆኑት በመምህር ክብረ አብ አማካኝነት የእምነት ገበሬ አምኃ ኢየሱስ ዘመን ከጎንደር ተነስተው ደቂት ሚካኤል በተተከለ በ2ኛ ዓመቱ በአንድ ቀን መቃኞ ሠርተው የእመቤታችንን ጽላቷን ያመጡ ሲሆን፤ የቅዱስ መርቆሬዎስን በ1817 ዓ.ም በአለቃ አፈወርቅ እና በደብተራ ሳሳሁ አማካይነት በተመሳሳይ ከጎንደር ማምጣታቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።
በጋዜጣዊው መግለጫ ላይ መጋቤ ሐዲስ ነቅዐጥበብ አባቡ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ መልአከ መንክራት ደምስ ድረሴ የደብሩ አስተዳዳሪ፣ መጋቤ ምሥጢር ፈቃዱ፣ አርቲስት ጸጋዬ እሸቱ፣ የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴዎች፣ የሕንጻው መሐንዲሶች እና ጥሪ የተደረገላቸው ግለሰቦች የተገኙ ሲሆን፤ በዚህ መርሐ ግብር የሰማዕቱን ጅምር ቤተክርስቲያን ከፍጻሜ ለማድረስ 70,000,00.00 [ሰባ ሚልዮን ብር] እንደሚያስፈልግ በመግለጥ በዕለቱ በአካል ከሚገኙ እና በሚዲያ አማራጭ ከሚከታተሉ ምዕመናን የታሰበውን ገንዘብ ለማሰባሰብ መታቀዱን አሳውቀዋል።
በዕለቱ በአካል ከ20,000 በላይ፣ ከ50,000 በላይ ምዕመናን በቀጥታ ሥርጭት ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የማዕዶት ለኢትዮጵያ እና የኢቲ አርት ሚዲያ ሥራ አስኪያጅ መምህር ምንያህል በንቲ የገለጡ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጀምራ በመጨረስ ትታወቃለች ያሉት ደግሞ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ነቅዐጥበብ አባቡ ናቸው።
ባለፉት 6 ወራት ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ለሚደረገው 12ኛው ማዕዶት ለኢትዮጵያ መርሐግብር ከጠቅላይ ቤተክህነት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላም እና ጸጥታ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም ከፌዴራል ፖሊስ አስፈላጊውን የፈቃድ ሥራዎች በመሥራት ለመርሐግብሩ የሚያስፈልገውን የፈቃድ ወረቀት መረከቡን አዘጋጆቹ አሳውቀዋል።
በዕለቱም ብፁዓን አበው ሊቃነጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ መምህራነ ወንጌል፣ ዘማርያን፣ ገጣሚያንና የጥበብ ሰዎች በአንድነት ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን፤ የመርሐ ግብሩ መግቢያ ትኬቶች አዲስ አበባ በሚገኙ በተመረጡ የአሐዱ ባንክ ቅርንጫፎች፣ በቴሌብር እና በተለያዩ ቦታዎች በመግዛት ምዕመናን ድጋፍ እንዲያደርጉ የተጠየቀ ሲሆን መርሐግብሩ ከቀኑ 6:00 ሰዓት ላይ እንደሚጀመር አዘጋጆቹ አሳውቀዋል።
በመጨረሻም ለሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ድጋፍ ማድረግ ለሚሹ፦
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000079751638 በአቢሲኒያ ባንክ 452282828 በዓባይ ባንክ 2701112903360022 ድጋፍ ማድረግና በ0911787825/ 0950252516/ 0950252519/ 0950252523 በመደወል መረጃዎች ማግነት እንደሚቻል ገልጸዋል።




