banner

ታክሲ ሞልተው ሿሿ ሲፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦች ተያዙ

#FastMereja I የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ በመምሰል የማታለል ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 9 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያጣራ መሆኑን የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገለፀ።

ተጠርጣሪዎቹ የማታለል (ሿሿ) ወንጀሉን ሲፈፅሙ የነበረው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ሲ.ኤም.ሲ አካባቢ ነው።

የግል ተበዳይን የት ነህ በማለት ከሲ.ኤም.ሲ ገስትሞል በመጫን የተወሰነ ርቀት እንደተጓዙ ሲ.ኤም.ሲ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (5 መቶ አፖርታማ) ጋር ሲደርሱ ትራፊክ አለ ውረድ ብለው የተሽከርካሪውን በር ከፍተው ገፍትረው ጥለው መሰወራቸውን የግል ተበዳይ ለሲ.ኤም.ሲ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ማመልከታቸውን ተከትሎ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ በተደረገው ጥረት በአራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ አካባቢ ሹፌርና ረዳት እንዲሁም ተሳፋሪ በመምሰል ወንጀሉን የሚፈፅሙ 9 ተጠርጣሪዎችን ለወንጀል መፈጸሚያ ከሚገለገሉበት የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2 ኦ/ሮ 78652 ተሽከርካሪ ጋር መያዛቸውን የሲ.ኤም.ሲ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ገልጿል፡፡

በግለሰቦቹ ላይ አስፈላጊውን ማስረጃ በማሰባሰብ ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን በመግለፅ በተመሳሳይ የማታለል ወይም የሿሿ ወንጀል የተፈፀመበት ማንኛውም ግለሰብ ሲ.ኤም.ሲ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ቀርቦ ወንጀል ፈፃሚዎቹን በመለየትና በመምረጥ ማስረጃ መስጠት የሚችል መሆኑ ተገልጿል።

ተጠርጣሪዎች በተሽከርካሪዎቻቸው ውስጥ ወንድና ሴት በመጫን አሟታል፣ ነፍሰ ጡር ናት፣ መስኮት ክፈት፣ ተባበራት እንዲሁም ትራፊክ መጣ ዝቅ በል በማለት በማዋከብ ከታክሲው ውረድ ሌላም ምክንያቶችን በመናገር ገፍትረው የሚያመልጡ በመሆኑ ህብረተሰቡ ለወንጀል ፈፃሚዎች ሰለባ ላለመሆን ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግና ከተፈፀመበትም የሰሌዳ ቁጥር የመያዝ ልምዱን ሊያጎለብት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መልዕክቱን አስተላልፏል።



Leave a Comment