#FastMereja I የአዋሽ ባንክ አ.ማ የባለአክሲዮኖች 30ኛ መደበኛ እና 18ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤዎች ዛሬ ህዳር 13 ቀን 2018 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል ተካሂዷል።
የአዋሽ ባንክ አ.ማ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጉሬ ኩምሳ የባንኩን ዓመታዊ ሪፖርት ለጠቅላላ ጉባኤው አቅርበዋል። እ.ኤ.አ በ2024/25 ሂሳብ ዓመት በራሱ እና በሀገሪቱ የግል ባንኮች ታሪክ ከፍተኛ የሆነውን ትርፍ መጠን ማስመዝገበን ገልጸዋል። ባንኩ ያስመዘገበው ውጤት ከቀደሙት ዓመታት እጅጉን የላቀና በየጊዜው የሚያስመዘግባቸው ተከታታይ ዕድገቶች ባንኩን በጠንካራና አስተማማኝ መሠረት ላይ እንዳቆሙት የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡
የአዋሽ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው በበኩላቸው በ2024/25 ሂሳብ ዓመት አዋሽ ባንክ እንደወትሮ ሁሉ በማህበረሰባችን ዉስጥ የሚከሰቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚያስከትሉትን ተፅዕኖዎችን ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል ብለዋል።
ከፋይናንስ አፈፃፀሞች ዕድገት አንጻር አዋሽ ባንክ በ2024/25 የሂሳብ ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ በተቀማጭ ገንዘብ እ.ኤ.አ ከ2023/24 ጋር ሲነጻጸር የ54 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ወይም የብር 125.9 ቢሊዮን ዕድገት በማስመዝገብ የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ሂሳብ ብር 358.4 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም በባንኩና በግል ባንኮች ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ዕድገት መሆኑ ተገልጿል።
በሂሳብ ዓመቱ ማጠቃለያ የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን ብር 442.6 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል እ.ኤ.አ ሰኔ 30 ቀን 2024 ከነበረበት ብር 20.3 ቢሊዮን የብር 7.6 ቢሊዮን ወይም የ37.2 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ እ.ኤ.አ ሰኔ 30 ቀን 2025 መጨረሻ ላይ ብር 27.9 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ ይህም ብሔራዊ ባንክ ነባር ባንኮች በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊደርሱበት ይገባል ብሎ ካስቀመጠው የካፒታል መጠን እጅጉን የሚበልጥ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ባንኩ በሂሳብ ዓመቱ ያስመዘገበው ያልተጣራ የትርፍ መጠን ብር 25.67 ቢሊዮን ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የብር 14.82 ቢሊዮን ወይም የ137 ከመቶ ዕድገት ማሳየቱና ይህም በግል ባንኮች ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ትርፍ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሂሳብ ዓመቱም ለሀገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ለመንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ለተለያዩ ድጋፍ ለሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎች በጤና፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በስራ ፈጠራ እና በመሳሰሉት የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ወደ 600 ሚሊዮን የሚጠጋ ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣቱን ገልጸዋል።




