#FastMereja I በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አስመጪነትና በኤክስፖርት ዘርፍ የተሰማራው ኢትዮፒካር (ETIOPIKAR)፤ በ20ኛው “ግራንድ አፍሪካ የአመራርና የተቋማት ሽልማት” ላይ በምርጥ ተቋማዊ አፈፃፀም ዘርፍ ሽልማት እንደተበረከተለት አስታውቋል።
ኩባንያው የተገኘውን ስኬት በማስመልከትም እስከ ጥምቀት በዓል የሚቆይ የዋጋ ቅናሽና የፋይናንስ አመቻች መርሃ-ግብር ይፋ አድርጓል።
ባለፈው ሳምንት በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም “ትጉኃንን እንሸልማለን” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው በዚሁ የሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ፤ ተቋሙ በሦስት የተለያዩ ዘርፎች እውቅናን አግኝቷል።
በዚሁ መሠረት የድርጅቱ መስራችና ባለቤት አቶ ሳሙኤል አዲስአለም በከፍተኛ አመራር ዘርፍ ሲሸለሙ፣ ሌሎች ሁለት የመካከለኛ አመራሮችም የላቀ አፈፃፀም ላሳዩ መሪዎች የሚሰጠውን ሽልማት ተቀብለዋል።
ተቋሙ ይህንን አህጉራዊ ስኬቱን ለደንበኞቹ ለማካፈል በሚል እስከ ጥምቀት በዓል የሚቆይ የዋጋ ቅናሽ ማድረጉን ገልጿል።
በተለይም ግለሰቦች እና ድርጅቶች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ ለማስቻል፤ የ50 በመቶ ቅድመ ክፍያ በመክፈል ቀሪውን ክፍያ ከተለያዩ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት ጋር በሚመቻች የብድር አገልግሎት መውሰድ የሚችሉበት አሰራር መዘርጋቱ ተመላክቷል።
እ.ኤ.አ በ2013 የቀድሞ የባንክ ባለሙያ በሆኑት በአቶ ሳሙኤል አዲስአለም የተመሰረተው “ሳሙኤል አዲስአለም አስመጪ እና ላኪ”፤ በአሁኑ ወቅት በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና በአዲስ አበባ ቅርንጫፎቹን በመክፈት በስፋት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ተቋሙ በኢትዮፒካር መለያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ከማስገባት ባለፈ፣ በቡና፣ በቅባት እህሎች እና በፍየል ስጋ ኤክስፖርት ዘርፍ በመሰማራት ለሀገር የውጭ ምንዛሬ ግኝት የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ከደረሰን መረጃ ለመረዳት ተችሏል።


