#FastMereja I የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት ከአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር ጋር በመተባበር፣ በዋና ከተማዋ ለሚገኙ ሆቴሎች የአገልግሎት አሰጣጥ ብቃታቸውን የሚያሳድግ ልዩ የማማከርና የቴክኒክ ድጋፍ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።
ባለፈው ሐሙስ በይፋ የተጀመረውን ይህንን አገራዊ ፋይዳ ያለው ስራ አስመልክቶ የኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም እና የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አስቴር ሰለሞን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
ይህ የማማከር አገልግሎት የተለመደው የንድፈ-ሀሳብ ስልጠና ሳይሆን፣ ባለሙያዎች በየሆቴሎቹ ተገኝተው የአሰራር ክፍተቶችን በተግባር የሚያርሙበት ነው። ለዚህም ስራ ከሁለቱ ተቋማት የተወጣጡ 12 ከፍተኛ ባለሙያዎችና ሱፐርቫይዘሮች የተመደቡ ሲሆን፣ በዚህ ዙር በየክፍለ ከተማው የሚገኙ 63 ባለኮከብ ሆቴሎችን እንዲያግዙ ይደረጋል።
ባለሙያዎቹ ከሆቴሎቹ ውጫዊ ገጽታ ጀምሮ የእንግዳ መቀበያ፣ የምግብ ዝግጅት፣ የመኝታ ክፍሎች አያያዝ እንዲሁም የምግብና መጠጥ መስተንግዶ ክፍሎችን በዝርዝር ይፈትሻሉ። በጽዳት አጠባበቅና በእንግዳ አቀባበል ላይ ክፍተቶች ሲገኙም “በቦታው ላይ የሚሰጥ ስልጠና” (On-the-spot training) በመስጠት ሰራተኞቹ እዛው እንዲማሩ ይደረጋል።
አገልግሎቱ አሁን እንዲጀመር የተደረገበት ወቅት ታሳቢ ያደረጋቸው ጉዳዮች እንዳሉ በመግለጫው ተጠቁሟል። በተለይም መጪውን የገና እና የጥምቀት በዓላትን ተከትሎ በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ወደ ሀገር ቤት የሚገቡበት ወቅት በመሆኑ፣ ሆቴሎች ደረጃቸውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል ቀዳሚው አላማ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በከተማዋ የሚስተናገዱ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በብቃት ለማስተናገድ የሆቴሎችን ዝግጁነት ከፍ ማድረግ የግድ መሆኑ ተገልጿል።
ፕሮግራሙ ሆቴሎችን ደግፎ ከመውጣት ባለፈ የአገልግሎቱን ውጤታማነት ለመመዘን የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶለታል።
የሆቴሎቹን የእርካታ ደረጃ የሚለካ ጥናት እንደሚደረግና በውጤቱም መነሻነት በቀጣይ የሚስተካከሉ ጉዳዮች ላይ ተከታታይ ድጋፍ እንደሚደረግ በመግለጫው ላይ ተነግሯል።




