#FastMereja I በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባሕር ዳር ከተማ ተወካይ የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ፣ በመጪው 7ኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ ራሳቸውን በእጩነት ላለማቅረብ መወሰናቸውን ዛሬ በይፋ ገለጹ።
የምክር ቤት አባሉ ውሳኔያቸውን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ያሰፈሯቸው ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦
ዶክተር ደሳለኝ ለውሳኔያቸው ዋነኛው ምክንያት “በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለው ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ” መሆኑን ገልጸዋል። ነፃ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ መደላድል አለመኖሩን የጠቀሱት አባሉ፣ በፓርላማ ውስጥ ለተጨማሪ አምስት ዓመታት መቆየታቸው “ለሕዝቡ የሚያበረክተው የረባ ጥቅም የሌለው መሆኑን” መረዳታቸውን አስታውቀዋል።
አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በባሕር ዳርም ሆነ በአዲስ አበባ በእጩነት እንዲቀርቡ ዕድል ሰጥተዋቸው እንደነበርና በግል የመወዳደርን አማራጭም ሲያመዛዝኑ እንደቆዩ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
የ6ኛው ዙር የፓርላማ የአገልግሎት ዘመናቸው እስከሚጠናቀቅበት እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ የሕዝብ እንደራሴነት ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ከሰኔ በኋላ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በምን መልኩ ማገልገል እንደሚፈልጉ ወደፊት ይፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ባለፉት ዓመታት ለሰጧቸው ድጋፍ ለባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎችና ለመላው የአማራ ሕዝብ ምስጋናቸውን በማቅረብ መግለጫቸውን አጠቃለዋል።
