banner

ልጁ ከአባቱ ጋር እንዲያድግ ፍርድ ቤት ወሰነ

#FastMereja I የአርቲስት ዮሴፍ ገብሬ (ጆሲ) የልጅ እናት የሆነችው ሶሲ ግርማይ፣ ለስድስት ወራት ያህል ሲካሄድ የቆየውን የልጅ አስተዳደግ ክርክር የፍርድ ቤት ውሳኔ ተከትሎ፣ መልዕክት አስተላልፋለች።

ሶሲ በፍርድ ሂደቱ ወቅት የቀረቡባትን ክሶች በሙሉ በምስክር እና በማስረጃ ብታፈርስም፣ ውሳኔው ግን “ከእናቴነት ይልቅ ለቁስ እና ለሀብት አድልቷል” ስትል ወቅሳለች።

​ሶሲ በመልዕክቷ ላይ እንደገለጸችው፣ በክሱ ወቅት “ሱሰኛ ነች፣ ባር ትሰራለች፣ አምሽታ ትገባለች፣ ልጇን ለገንዘብ መጠየቂያ አድርጋለች” የሚሉ ከባድ ስም ማጥፋቶች ቀርበውባት እንደነበር ተናግራለች። ሆኖም፡-
​የስራ ባህሪዋ የባልትና ውጤቶችን ማዘጋጀት እንደሆነ በጎረቤቶቿ ተመስክሯል። ​ምንም አይነት ሱስ እንደሌለባትና ለልጆቿ መልካም እናት መሆኗ በምስክር ተረጋግጧል።
​አባትየው (አርቲስት ዮሴፍ) ለልጁ ትምህርት ቤት ክፍያ እንደማይከፍል፣ እንዲያውም በትምህርት ቤቱ እንደማይታወቅ በትምህርት ቤቱ መረጃ መረጋገጡን ገልጻለች።

​ሶሲ እንደገለጸችው፣ የሶሻል ወርከሮቹ ያቀረቡት ሪፖርት እሷ ካቀረበችው የሞራል እና የእናትነት ብቃት ይልቅ፣ በአባትየው ቁሳዊ አቅም ላይ ያተኮረ ነበር ብላለች።

​”የሱ ገቢ ከሷ ይበልጣል፣ የሱ ቤት ትልቅ ነው፣ የልጁ መኝታ ቤት አለው፣ ሰፈራቸው ቦሌ ነው፣ መጫወቻ ብዙ አለው” የሚሉ ነጥቦች በውሳኔው ላይ ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸው ጠቁማለች።

​በዚህም ምክንያት ፍርድ ቤቱ ልጁ ከአባቱ ጋር እንዲያድግ የወሰነ ሲሆን፣ እናትየው በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ እሁድ ዕለት ብቻ ለጥቂት ሰዓታት እንድትጎበኝ ተፈቅዶላታል።

​ሶሲ አሁን ያለችበትን የጤና እና የስነ-ልቦና ሁኔታ ስትገልጽ “ሆስፒታል ተኝቼ ነው የምፅፈው” ብላለች። እናትነት ከቤት እና ከመኪና አኳያ ተመዝኖ ዝቅ መደረጉ እጅግ እንደሰበራትና አሁንም ፍርዱን ለፈጣሪ እንደምትተው ገልጻለች።

​በመጨረሻም፣ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ከጎኗ ለቆመችው ጠበቃዋ ሰብለ አሰፋ እና ለጸለዩላት ወዳጆቿ ምስጋናዋን አቅርባ፣ “አሁን ደክሞኛል፣ ልረፍ” ስትል መልዕክቷን ደምድማለች።

Leave a Comment