banner

ማስተዋል ቼዝ አካዳሚ በይፋ ተመረቀ!

#Fastmereja: የልጆችንና የአዋቂዎችን የስትራቴጂያዊ አስተሳሰብ እና የፈጠራ አቅም ለማሳደግ ያለመው “ማስተዋል የአዕምሮ ማበልፀጊያ ተቋም” በአዲስ አበባ አያት አካባቢ ዘመናዊ የቼዝ አካዳሚ ዛሬ በደመቀ ሁኔታ አስመርቋል።

በአዳማ ከተማ በ2015 ዓ.ም የተመሠረተው ማስተዋል የአዕምሮ ማበልፀጊያ ተቋም አሁን በአዲስ አበባ ተመርቆ ስራ በጀመረዉ የቼዝ አካዳሚ እድሜዉ ከ8 አመት ጀምሮ ያለ ሰዉ መሰልጠን እንደሚችል ተገልጿል።

ቼዝ ተራ ጨዋታ ሳይሆን የአዕምሮ ስፖርት መሆኑን እና ተቋሙ ቼዝን እንደ መሣሪያ የመረጠዉ የፈጠራ አስተሳሰብን ስለሚያዳብር፣ትኩረትን እና ትዕግስትን ስለሚያስተምር፣ ለአዕምሮ ጤና እና ለማህበራዊ እሴት ግንባታ ወደር ስለሌለው እንደሆነ ተገልጿል።

የአካዳሚው መስራች አቶ ፈለቀ ጌታቸው፣ ዓላማቸው ከመላው ዓለም ሰልጣኞችን የሚቀበል በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ግዙፍ ተቋም መገንባት እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቼዝ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ተሾመ በቀለ እንደገለጹት የነገ ግራንድ ማስተሮች መፍለቂያ ይሆናል ያሉት ይህ ተቋም ለሀገራችን የነገ የቼዝ ኮከቦችን (Grandmasters) ለማፍራት ትልቅ ተስፋ ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።

ማስተዋል የቼዝ አካዳሚ ትርፍን ብቻ ሳይሆን ማህበረሰባዊ አገልግሎትንም ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ እና ለተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ነፃ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።

ተቋሙ በአካባቢ ደረጃ ብቻ ሳይወሰን፣ በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ እና ከመላው ዓለም ሰልጣኞችን ተቀብሎ የሚያስተናግድ ግዙፍ የቼዝ ማዕከል የመሆን ራዕይ እንዳለዉም በመክፈቻዉ ተገልጿል።





Leave a Comment