banner

በቴክኖሎጂ የታገዘው የጤና መረጃ አያያዝ በይፋ ተጀመረ!

#Fastmereja I የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ስርዓትን የሚያዘምን ዲጂታል አሰራር ይፋ የሚደረግበት መድረክ በዛሬዉ እለት አካሂዷል፡፡

ይህ መድረክ ”የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስርዓትን በማዘመን፤ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር የልህቀት ማዕከል እቅድን ለማሳካት” በሚል መሪ ቃል የተመራ ሲሆን፣ በዘርፉ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ ተግባራት ተከናዉኗል።

በአዲስ መልክ የተደራጀውና እጅግ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሰራርን የተላበሰው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከልም በይፋ ተመርቋል።

ማዕከሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የጤና ስጋቶችን በንቃት ለመከታተልና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንደ ዋና የቁጥጥር ማማ ሆኖ እንደሚያገለግል ተገልጿል።

እንዲሁም ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ የICT መሣሪያዎች ለክልል ጤና ቢሮዎች የተሰራጩ ሲሆን ከ3,900 በላይ ላፕቶፕና ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች እንዲሁም የተለያዩ ቁሳቁሶች ለክልል የጤና መዋቅሮች መሰራጨቱ ተገልጿል።

ይህ ድጋፍ ክልሎች መረጃን በወቅቱ እንዲያስተላልፉና ወረርሽኞችን ገና በጅምራቸው እንዲለዩ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርላቸዉም ነዉ የተገለፀዉ።

ይህ ታላቅ ንቅናቄ ኢትዮጵያ እንደ ኮቪድ-19 እና ሌሎች ወረርሽኞች ያሉ ድንገተኛ አደጋዎችን አስቀድማ ለመለየትና የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ያላትን ዝግጁነት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድገዋል ሲሉ ገልፀዋል።

እነዚህ የቴክኖሎጂ ግብዓቶቹ መሰራጨታቸው ደግሞ የጤና መረጃ አያያዛችንን ከወረቀት ወደ ዲጂታል በማሸጋገር የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱን ያፈጥነዋል።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር እያከናወነ ያለው ይህ ተግባር የሀገሪቱን የጤና ሴክተር የልህቀት ማዕከል(Center of Excellence) ለማድረግ የተያዘውን ግብ የሚያሳካ መሆኑ ታምኖበታል።

በመርሐ ግብሩ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።





Leave a Comment