#FastMereja I ላለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ደማቅ አሻራ ያሳረፈው አንጋፋው አምባሰል ሙዚቃ ቤት፣ በአዲስ አደረጃጀትና በዘመናዊ ይዘት ዳግም ስራ መጀመሩን አበሰረ። አምባሰል ስራውን የጀመረውም በበርካታ የሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ ተስፋ የተጣለበትን የወጣቱ ድምፃዊ ብስራት አለማየሁ የበኩር አልበም ለህዝብ በማቅረብ ነው።
“ደስታ ለኔ” የጥበብ ስራው
በኤንቢሲ ኢትዮጵያ ታለንት ሾው ተሸላሚና በባላገሩ አይዶል “እደግ ተመንደግ” የተባለለት ድምፃዊ ብስራት አለማየሁ፤ “ደስታ ለኔ” የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበሙን በዚህ ሳምንት መጨረሻ በአምባሰል የዩቲዩብ ቻናል ላይ ይለቃል።
አልበሙ 10 ተመረጡ ትራኮችን የያዘ ሲሆን፣ የሚከተሉትን ዋና ዋና ጭብጦች ያካተተ ነው፦
• ማህበራዊ ጉዳዮችና ፍቅር
• ሀገራዊ አንድነትና መከባበር
• ዘመናዊ የአዘፋፈን ስልት ከጥንታዊ ቅላፄ ጋር የተዋሃደበት
ከጀርባ ያሉ የጥበብ ባለሙያዎች
የአልበሙ ዝግጅት በሀገራችን ስመ-ጥር የሙዚቃ ባለሙያዎች ጥበባዊ አሻራ ያረፈበት ሲሆን፦
• የሙዚቃ ቅንብር፦ እዮብ ባልቻ፣ ማቲ ማን እና ሳሚ ዮባል
• ግጥምና ዜማ፦ ኤፍሬም አበበ (ከፍ ከፍ)፣ መስፍን ከበደ፣ ዜና ታደሰ እና ድምፃዊው ብስራት አለማየሁ
• ሚክሲንግና ማስተሪንግ፦ ታደለ ማንያህልሃል (Big T)
• መሳሪያ ተጫዋቾች፦ ፍራኦል ተመስገን፣ ዮናስ ለማ እና ፍሬህይወት ቴዎድሮስ
ድምፃዊ ብስራት አለማየሁ ከልጅነቱ ጀምሮ በብስራተ ገብርኤል ሰንበት ትምህርት ቤት በዝማሬ ማገልገሉ ለተስረቅራቂ ድምፅና ለጥልቅ የሙዚቃ ቅላፄ ባለቤት እንዲሆን መሰረት ሆኖታል። በተለያዩ መድረኮች እንደ አንጋፋዎቹ ጥላሁን ገሰሰ፣ አለማየሁ እሸቴ እና ቴዎድሮስ ታደሰ ያሉ የጥበብ ሰዎችን ስራዎች በማንቆርቆር የአድናቆት ናፍቆትን ሲያረካ ቆይቷል።
ጋዜጠኛ ሲሳይ መንግስቴ


