#FastMereja I የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፣ ኢራን የተዳከመውን የኑክሌርና የሚሳይል አቅሟን ዳግም ለመገንባት “እያሴረች ነው” ሲሉ ወነጀሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም በአሁኑ ወቅት በአፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ ኢራን ወደፊት “ሊደፈር የማይችል” አቅም ባለቤት ትሆናለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ይህን መግለጫ የሰጡት አሜሪካና እስራኤል በኢራን ወታደራዊ ተቋማት ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እያደረሱ ባሉበት ወቅት ነው። ኔታንያሁ በንግግራቸው፣ የኢራን ገዥ አካል አሁንም የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን ባለቤት ለመሆን ያለውን ፍላጎት እንዳልተወ ገልጸው፤ ይህ ደግሞ ለቀጣናውም ሆነ ለዓለም ደህንነት ትልቅ ስጋት መሆኑን አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወታደራዊ ማስጠንቀቂያው በተጨማሪ፣ ለኢራን ሕዝብ ቀጥተኛ የፖለቲካ መልዕክት አስተላልፈዋል። ኢራናውያን አሁን ያለውን ሥርዓት በማስወገድ “አዲስና ነጻ የሆነች ኢራንን እንዲመሠርቱ” ጥሪ አቅርበዋል።
ኔታንያሁ ለኢራን ዜጎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ “ዕድላችሁን በገዛ እጃችሁ ያዙ” ሲሉ አሳስበዋል። ይህም የኢራን ሕዝብ በሀገሩ ላይ ለውጥ እንዲያመጣና ከእስላማዊ ሪፐብሊኩ አገዛዝ ነጻ እንዲወጣ ግፊት ለማድረግ የታለመ ንግግር መሆኑ ተመልክቷል።
ይህ የኔታንያሁ ንግግር በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ ያለውን ወታደራዊ ግጭት ወደ ላቀ የፖለቲካ ፍጥጫ ያሸጋገረው ሲሆን፣ እስራኤል በኢራን ላይ የምታደርገው ጥቃት ወታደራዊ መሠረተ ልማቶችን ከማውደም ባለፈ በሀገሪቱ የሥልጣን ለውጥ እንዲመጣ የመፈለግ አዝማሚያ እንዳለው ያሳያል ተብሏል።
