banner

በአሜሪካ “ንጉሥ አንፈልግም” ያሉ ግዙፍ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሄዱ

​#FastMereja I በአሜሪካ ዋና ዋና ከተሞችና በውጭ አገራት በሚኖሩ አሜሪካውያን ዘንድ “ንጉሥ አንፈልግም” በሚል መሪ ቃል በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ላይ ያነጣጠሩ ግዙፍ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሄዱ። ሰልፈኞቹ የትራምፕን የኢራን ፖሊሲ፣ የስደተኞች አያያዝ እና የኑሮ ውድነትን በመቃወም ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን እንዲወርዱ መጠየቃቸው ተረጋግጧል።

ቅዳሜ ዕለት በዋሽንግተን ዲሲ፣ ኒውዮርክ፣ ሎስ አንጀለስ እና ሚኒሶታ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አደባባይ ወጥተዋል። በተለይም በሚኒሶታ በፌዴራል ወኪሎች የተገደሉ ሁለት ዜጎችን መታሰቢያ በማድረግ የተካሄደው ሰልፍ ከፍተኛ ትኩረት ስቧል። በኒውዮርክ ታይምስ አደባባይ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች መገኘታቸውን የከተማዋ ፖሊስ አስታውቋል።

በሎስ አንጀለስ ሰልፈኞች የፌዴራል ሕንጻን በመክበብ ድንጋይ በመወርወራቸውና ፖሊስን በመተናኮላቸው “ገዳይ ያልሆኑ እርምጃዎች” መወሰዳቸውንና በርካቶች መታሰራቸውን የሀገር ውስጥ ደህንነት መምሪያ (DHS) ገልጿል። በዳላስም በተቃራኒ ሰልፈኞችና በ”ንጉሥ አንፈልግም” ደጋፊዎች መካከል መጠነኛ ግጭቶች ተከስተዋል።

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ሰልፎቹን “ከትራምፕ ጋር ችግር ያለባቸው ሰዎች ራሳቸውን የሚያክሙበት መድረክ” ሲሉ አጣጥለውታል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ በበኩላቸው “ንጉሥ አይደለሁም” በማለት የሚሰነዘርባቸውን የአምባገነንነት ክስ ቀደም ብለው ማስተባበላቸው ይታወሳል።

ተቃውሞው ከአሜሪካ አልፎ በፓሪስ፣ ለንደን እና ሊዝበን በሚኖሩ አሜሪካውያን ዘንድ የቀጠለ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱን “ፋሺስት” እና “የጦር ወንጀለኛ” የሚሉ መፈክሮች ተደምጠዋል።

Leave a Comment