banner

ሁለት የነዳጅ ጫኝ መርከቦች የሆርሙዝ ወሽመጥን በሰላም ተሻገሩ

​#FastMereja I በሆርሙዝ ወሽመጥ አካባቢ የሚታየው የባህር ላይ ትራንስፖርት መስተጓጎል በከፍተኛ ሁኔታ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት፣ ሁለት የህንድ የፈሳሽ ጋዝ (LPG) ጫኝ መርከቦች ቀጠናውን በሰላም ማለፋቸው ተረጋግጧል። BW TYR እና BW ELM የተሰኙት እነዚህ መርከቦች በአጠቃላይ 94,000 ቶን ጋዝ ጭነው ወደ ሙምባይ እና ኒው ማንጋሎር ወደቦች በመጓዝ ላይ ይገኛሉ ሲል ኩዌት ታይምስ ዘግበዋል።

​በቀጠናው ባለው የጸጥታ ስጋት ምክንያት የዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ ተገትቶ በቆየበት በዚህ ወቅት፣ የህንድ መርከቦች ጉዞ ስኬታማ መሆን ለሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት ትልቅ እፎይታ ተደርጎ ተወስዷል። ቀደም ሲል አራት ሌሎች የህንድ መርከቦች ተመሳሳይ መስመር ተጠቅመው ያለፉ ቢሆንም፣ አሁንም 485 የህንድ ዜጎችን የያዙ 18 መርከቦች በባህረ ሰላጤው ቀጠና ውስጥ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

​ህንድ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የምትጠቀመውን የፈሳሽ ጋዝ አብዛኛውን የምታስመጣው ከመካከለኛው ምስራቅ እንደመሆኑ መጠን፣ አሁን ያለው መስተጓጎል በጋዝ አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም።

በዚህም ምክንያት መንግስት የጋዝ ስርጭትን በበላይነት ለመቆጣጠር ጥብቅ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል። ሀገሪቱ ከአቅርቦት መቆራረጥ ጋር እየታገለች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ ከኢራን እና ከእስራኤል ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በንቃትና በሚዛናዊነት ለመያዝ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።

​መጋቢት 20 ቀን 2018 ዓ.ም

Leave a Comment