banner

የኬፕ ታውን አውሮፕላን ማረፊያ የአፍሪካ ቁንጮነቱን አረጋገጠ።

​#FastMereja I የደቡብ አፍሪካው ኬፕ ታውን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለ11ኛ ተከታታይ ዓመት የአፍሪካ ምርጥ አውሮፕላን ማረፊያ ተብሎ መመረጡን ስካይትራክስ (Skytrax) ይፋ ባደረገው የ2026 የዓለም አውሮፕላን ማረፊያዎች ደረጃ አመላክቷል። የኢትዮጵያው አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በዘንድሮው ዝርዝር ውስጥ 9ኛ ደረጃን ይዟል።

​በለንደን በተካሄደው የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው፣ የኬፕ ታውን አውሮፕላን ማረፊያ ከአህጉራዊው የበላይነት በተጨማሪ “በአፍሪካ ምርጥ የሰራተኞች አገልግሎት” እና “በአፍሪካ ንጹህ አውሮፕላን ማረፊያ” የሚሉ ተጨማሪ ሽልማቶችን መውሰድ ችሏል። ደረጃው የተሰጠው ከመላው ዓለም የተውጣጡ መንገደኞች በአገልግሎት ጥራት፣ በመሰረተ ልማት እና በአጠቃላይ የጉዞ ልምድ ላይ በሰጡት ግብረ-መልስ መሠረት ነው።

​በዘንድሮው የ2026 ደረጃ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆኑት 10 አውሮፕላን ማረፊያዎች የሚከተሉት ናቸው፦
1ኛ ​ኬፕ ታውን (ደቡብ አፍሪካ)
2ኛ ​ኦ.አር ታምቦ/ጆሃንስበርግ (ደቡብ አፍሪካ)
3ኛ ​ማራኬሽ ሜናራ (ሞሮኮ)
4ኛ ​ኪንግ ሻካ/ደርባን (ደቡብ አፍሪካ)
5ኛ ​መሐመድ አምስተኛ/ካዛብላንካ (ሞሮኮ)
6ኛ ​ካይሮ (ግብፅ)
7ኛ ​ሰር ሲውሳጉር ራምጉላም (ሞሪሸስ)
8ኛ ​ኪጋሊ (ሩዋንዳ)
9ኛ ​አዲስ አበባ ቦሌ (ኢትዮጵያ)
10ኛ ​ኢቫቶ/አንታናናሪቮ (ማዳጋስካር)

​በዓለም አቀፍ ደረጃ የሲንጋፖሩ ቻንጊ አውሮፕላን ማረፊያ የዓመቱ ምርጥ በመሆን ቀዳሚነቱን ሲይዝ፣ የደቡብ አፍሪካዎቹ ኬፕ ታውን (74ኛ) እና ኦ.አር ታምቦ (84ኛ) ብቻ ከዓለም 100 ምርጥ አውሮፕላን ማረፊያዎች ውስጥ መካተት የቻሉ አህጉራዊ ተቋማት ሆነዋል። የኬንያው ጆሞ ኬንያታ አውሮፕላን ማረፊያ በዘንድሮው የአስርቱ ዝርዝር ውስጥ ሳይካተት ቀርቷል።

​መጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም

Leave a Comment