banner

ሚሊዮኖች የሚሳተፉበት የታላቁ የትንሳኤ በዓል እና የ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሀገራዊ ጸሎት መርሐ-ግብር ተዘጋጀ!

#FastMereja I የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት የምስረታውን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ እና የዘንድሮውን የትንሳኤ በዓል በማስመልከት፣ በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ ስቴዲየም ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ እንደሚያካሂድ በዛሬዉ እለት አስታዉቋል።

ይህ በዓል ከሃይማኖታዊ ስነ-ሥርዓት ባለፈ፣ መጪው 7ተኛዉ ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ”የአደባባይ ጸሎት” የሚደረግበት መድረክ እንደሆነም ተገልጿል።

የግማሽ ክፍለ ዘመን ጉዞ እና የወርቅ ኢዮቤልዩ ህብረቱ በ1968 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የመጀመሪያውን ጉባኤ ካካሄደበት ጊዜ አንስቶ ያለፈባቸውን አምስት አስርት ዓመታት ለመዘከር ልዩ ዝግጅቶችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

የህብረቱ ፕሬዝዳንት ፓስተር ደረጀ ታፈሰ እንደገለፁት ዋናው የኢዮቤልዩ በዓል በሐምሌ ወር የሚከበር ቢሆንም፣ የፊታችን ሚያዚያ 4 ቀን 2018 ዓ.ም የሚከበረው የትንሳኤ በዓል የዚህ ታሪካዊ ጉዞ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

በዕለቱ የህብረቱን ምስረታ የሚዘክሩ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽኖች እና የታሪክ ምስክርነቶች ለምዕመኑ እንደሚቀርቡ ታውቋል።

ፓስተር ደረጀ “መጪው ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ አደባባይ ላይ ወጥተን ጸሎት እናደርጋለን” ሲሉ የገለጹ ሲሆን፣ ቤተክርስቲያን ለሀገር መረጋጋትና ለአንድነት ያላትን ኃላፊነት በይፋ እንደምትወጣ አረጋግጠዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም፣ በሃይማኖትና በብሔር ስም የሚነሱ የጥልና የመለያየት አስተምህሮዎችን ህብረቱ በጽኑ እንደሚቃወም ገልጸው፤ “እውነተኛው የወንጌል አስተምህሮ ሰላምና ፍቅር እንጂ መቃቃር አይደለም” ብለዋል፡፡

ህብረቱ “ትንሳኤና ሕይወት እኔ ነኝ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መሪ በማድረግ፣ በዕለቱ የተቸገሩ ወገኖችን የመርዳትና የማዕድ ማጋራት መርሐ-ግብር አዘጋጅቷል። ይህ ልማድ ህብረቱ በየዓመቱ በታላላቅ በዓላት የሚያከናውነው ማህበራዊ አገልግሎት መሆኑ ተጠቅሷል።

ሚያዚያ 4 ቀን ከማለዳው 12:00 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ስቴዲየም በሚካሄደው በዚህ ታላቅ መርሐ-ግብር ላይ፣ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማኞች እንዲገኙ ጥሪ ተላልፏል።





Leave a Comment