banner

በወላይታ ሶዶ ቅዱስ መጽሐፍን ለንግድ መጠቅለያነት ሲጠቀም የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

#FastMereja I በወላይታ ሶዶ ከተማ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾችን በመቅደድ ለብስኩት መጠቅለያነት ሲጠቀም የተገኘ ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጠ። ድርጊቱ በከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የታለመ ቢሆንም፣ ማህበረሰቡ በሰላማዊ መንገድ ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ያሳየው ጨዋነት ተመስግኗል።

ትላንት መጋቢት 23 ቀን 2018 ዓ.ም በወላይታ ሶዶ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ህብረት ቀበሌ ውስጥ አቶ ሽኩር መሃመድ የተባለ በሻይ ቤት ንግድ ስራ የሚተዳደር ግለሰብ፣ የቅዱስ መጽሐፍ ገጾችን በመቅደድ ብስኩት ሲጠቀልልና ሲሸጥ መገኘቱን የከተማው ፖሊስ አስታውቋል። ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ግለሰቡን ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያካሄደ ይገኛል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ባወጣው መግለጫ እንደጠቆመው ግለሰቡ ለዚሁ ድርጊት ፈጻሚነት ህጻን ልጅ ሲጠቀም እንደነበረ ተረጋግጧል። የንግድ ስፍራው በፖሊስ የታሸገ ሲሆን፣ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተጨማሪ ፍተሻዎች እየተካሄዱ ነው። ድርጊቱ በሃይማኖቶች መካከል ያለውን የመቻቻል እሴት ለመናድ የታቀደ የሁከት ሙከራ መሆኑ ተገልጿል።

ፖሊስ የከተማው ነዋሪዎች በጉዳዩ ሳይቆጡ በሰላማዊ መንገድ ለህግ የበላይነት በሰጡት ቅድሚያ ምስጋናውን ያቀረበ ሲሆን፣ የምርመራ ውጤቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ማህበረሰቡ በትዕግስት እንዲጠባበቅ አሳስቧል። ማንኛውንም ሁከት ሊፈጥሩ የሚችሉ አካላትን በመከላከል ረገድ ህዝቡ ከጸጥታ አካላት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት ተላልፏል።

መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም
ወላይታ ሶዶ፣ ኢትዮጵያ

Leave a Comment