#FastMereja I ለገንዘብ እና ለንብረት ሲል ፍቅረኛውን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለው ብሩክ ደጀን የተባለ ግለሰብ፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት።
ተከሳሹ ብሩክ ደጀን ሟች ጥጋብ ሙላትን “የፍቅር ጓደኛዬ ትሆኛለሽ” በሚል ሰበብ ከቀረባት በኋላ፣ ዓላማው በባንክ ያላትን ገንዘብና ስልኳን መዝረፍ እንደነበረ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ያሳያል። ወንጀሉን ለመፈጸም እንዲመቸው “ታመሙ ቤተሰቦችን ባህር ዳር ሄደን እንጠይቅ” በማለት ከሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ከቤቷ ይዟት ወጥቷል።
ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ከሌሊቱ 11 ሰዓት ገደማ፣ ሟችን ወደ አንድ ጫካ በመውሰድ በፌሮ ብረት ጭንቅላቷን በተደጋጋሚ በመምታት ህይወቷ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲያልፍ አድርጓል።
ተከሳሹ ግድያውን ከፈጸመ በኋላ የሟችን የኢንፊኒክስ (Infinix) ስልክ፣ በባንክ አካውንቷ የነበረ 465,214 ብር በሞባይል ባንኪንግ አስተላልፏል፣ በሟች ስልክ ለወንድሟ በመደወል “ፀበል ቦታ ነኝ” በሚል ማታለያ የተቀበለው 86,000 ብር፣ የሟች ቤተሰቦች በሁኔታው ተጠራጥረው መስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ መሰረት ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ውሏል። ፍርድ ቤቱ የቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ መርምሮ ተከሳሹ ወንጀሉን መፈጸሙን በማረጋገጡ፣ መጋቢት 25 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት የ25 ዓመት ፅኑ እስራት ውሳኔ አስተላልፎበታል።
