#FastMereja I የኢራን አብዮታዊ ዘበ (IRGC) የደህንነት ቢሮ ሃላፊ ሜጀር ጄኔራል ማጂድ ካዴሚ በዛሬው ዕለት በተሰነዘረ የአየር ጥቃት መገደላቸውን የሀገሪቱ መንግስታዊ መገናኛ ብዙኃን አረጋገጡ።
በቴህራን በተፈጸመው በዚህ ጥቃት ጄኔራል ማጂድ ካዴሚ መገደላቸውን የአብዮታዊ ዘበኛው ይፋዊ መግለጫ ጠቅሶ “ታስኒም” የዜና ወኪል ዘግቧል። እንደ ዘገባው ከሆነ ጥቃቱ የተፈጸመው ዛሬ ሰኞ ጎህ ሲቀድ ሲሆን፣ ለግድያው “የአሜሪካ እና እስራኤል ጥምረት” ተጠያቂ መሆኑን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ሜጀር ጄኔራል ካዴሚ በፈረንጆቹ ሰኔ 2025 ነበር የቀድሞውን የደህንነት ሃላፊ ሞሃመድ ካዜሚን በመተካት ለዚህ ከፍተኛ ኃላፊነት የተሾሙት። ካዜሚም በተመሳሳይ መልኩ ባለፈው ዓመት በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደላቸው ይታወሳል።
ጄኔራል ካዴሚ ከአብዮታዊ ዘበኛው የደህንነት መዋቅር በተጨማሪ፣ በሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ የመረጃ ጥበቃ ድርጅትን በመምራት ለረጅም ዓመታት ከፍተኛ ወታደራዊ እና የደህንነት ልምድ ያካበቱ አንጋፋ መኮንን ነበሩ። ጥቃቱን ተከትሎ እስካሁን ከአሜሪካም ሆነ ከእስራኤል ወገን የተሰጠ ይፋዊ ምላሽ የለም።
ይህ ግድያ በክልሉ እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት ወደ አዲስ ምዕራፍ ሊያሸጋግረው እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
