#FastMereja I በብሔራዊ ሙዚየም የትኬት ሽያጭ ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ ጌራወርቅ አሰፋ፣ አንድ ቻይናዊ ጎብኝ የዘነጋውን 47 ሺህ ብር የያዘ ቦርሳ በታማኝነት በመመለስ የሀገርን ገጽታ የሚያስከብር ተግባር ፈጽመዋል።
የካቲት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ሶንግ ጆንግ የተባለ ቻይናዊ ጎብኝ ከጓደኞቹ ጋር በብሔራዊ ሙዚየም ያደረገውን ጉብኝት አጠናቆ ሲወጣ፣ 47 ሺህ የኢትዮጵያ ብር የያዘ ቦርሳውን ዘንግቶት ነበር። ቦርሳው የወደቀው በትኬት መቁረጫ መስኮት አካባቢ ሲሆን፣ ወ/ሮ ጌራወርቅ አሰፋ ቦርሳውን እንዳገኘች ለባልደረቦቿ በማሳወቅ በጥንቃቄ ጠብቃ እንዲቆይ አድርጋለች።
ከአራት ሰዓታት በኋላ ቻይናዊው ጎብኝ በከፍተኛ ጭንቀት ወደ ሙዚየሙ ቢመለስም፣ የጠፋበትን ገንዘብ አንድም ሳንቲም ሳይጎድል ተረክቧል። ወ/ሮ ጌራወርቅ ለኤኤምኤን (AMN) በሰጠችው ቃል፣ “ገንዘቡን ስመልስ ከእሱ በላይ ትልቅ ሸክም እንደወረደልኝ ተሰምቶኝ እፎይታ አግኝቻለሁ” ስትል ገልጻለች።
ጎብኚው ሶንግ ጆንግ በኢትዮጵያውያን ቅንነት እጅግ መገረሙን በመግለጽ፣ የወ/ሮ ጌራወርቅን ታማኝነት የሚገልጽ የምስጋና ማስታወሻ በገዛ እጁ አስፍሯል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የብሔራዊ ሙዚየም መሪ ስራ አስፈፃሚ፣ ለባለሙያዋ የምስጋና ደብዳቤና እውቅና መስጠታቸውን አስታውቀዋል። ይህ ተግባር በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ትልቅ የሥነ-ምግባር አርአያ ተደርጎ ተወስዷል።
