#FastMereja I የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት (IDF) በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኝን የኢየሱስ ክርስቶስን ሃውልት ሲሰብር የሚያሳይ የፎቶ መረጃ ትክክለኛ መሆኑን አረጋገጠ። ድርጊቱ የተፈጸመው በደብል በተባለች የክርስቲያን መንደር ውስጥ ሲሆን፣ ተያያዥነት ባላቸው ወታደሮች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ሰራዊቱ አስታውቋል።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት እየተሰራጨ የመጣው ይህ ምስል፣ አንድ የእስራኤል ወታደር በቅርቡ በሊባኖስ ውስጥ በሚካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ወቅት በመዶሻ የክርስቶስን ስቅለት ሲያፈርስ ያሳያል። የኢየሱስ ክርስቶስን ሃውልት የማፈራረሱ ድርጊት የተፈጸመው በሊባኖስ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው እና የክርስትና እምነት ተከታዮች በብዛት በሚኖሩባት ደብል ከተማ ውስጥ መሆኑ ተገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ባወጣው መግለጫ፣ ድርጊቱን የፈጸመውን አካል መለየቱንና በሰሜን እዝ በኩል “ተገቢው እርምጃ እንደሚወሰድ” አስታውቋል። ድርጊቱ በከተማዋ ነዋሪዎችና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን እየቀሰቀሰ ይገኛል። በተለይም በሲቪል አካባቢዎች በሚደረጉ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ወቅት መሰል የኃይማኖት ምልክቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የጦርነቱን ስነ-ምግባር የሚጥሱ መሆናቸውን የዘርፉ ተከታታዮች እየገለጹ ነው።
