banner

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መኪና ዋጋ መናር፣ የገዢዎች እውቀት ማነስ

​#FastMereja I በኢትዮጵያ የናፍጣ እጥረትን ተገን በማድረግ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ መደረጉ ተሰማ። ገዢዎች ስለ ገበያው ተለዋዋጭነት ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን እና ወቅታዊውን የነዳጅ እጥረት በመፍራት እያሳዩት ያለው መርበድበድ፣ ለመኪና ሻጮች ዋጋን ያላግባብ ለመቀየር አመቺ ሁኔታ መፍጠሩ ተነግሯል።

​በሀገሪቱ ተከስቶ ባለው የናፍጣ አቅርቦት መስተጓጎል ምክንያት፣ ብዙዎች አማራጭ ፍለጋ ወደ ኤሌክትሪክ መኪናዎች ፊታቸውን አዙረዋል። ይሁን እንጂ ይህ ፍላጎት በታቀደ እና በሰከነ መንገድ ከመመራት ይልቅ፣ በድንገተኛ ስጋት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የዋጋ ግሽበቱን አባብሶታል። መኪና ሻጮች የገዢዎችን ስጋት በመጠቀም፣ በአንድ ሌሊት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር በዋጋው ላይ እየጨመሩ እንደሚገኙ በዘርፉ ያሉ ታዛቢዎች ገልጸዋል።

​የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት፣ አሁን በኤሌክትሪክ መኪናዎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ከምርት እጥረት ወይም ከታክስ ለውጥ የመጣ ሳይሆን፣ በገዢዎች “ጊዜያዊ ስጋት” የተፈጠረ ነው። ገዢዎች የነዳጅ እጥረቱ መፍትሔ ሲያገኝ የኤሌክትሪክ መኪናዎች ዋጋ ወደ ቀድሞው ሊመለስ እንደሚችል ካለመገንዘባቸውም በላይ፣ በቂ የገበያ ጥናት ሳያደርጉ ወደ ግዢ እየገቡ መሆኑ ለሻጮች አላስፈላጊ ትርፍ በር ከፍቷል።

​በአሁኑ ወቅት በገበያው ላይ የሚታየው የዋጋ መጋነን ለዘላቂው የኤሌክትሪክ መኪና ሽግግር እንቅፋት ሊሆን እንደሚችልም ተሰግቷል። የዘርፉ ባለሙያዎች ገዢዎች ተረጋግተው ገበያውን እንዲቃኙ እና ሻጮችም ወቅታዊ ችግሮችን ለግል ጥቅም ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።

Leave a Comment