0
#FastMereja I ፖለቲከኛና አክቲቪስት ጀዋር መሐመድ 40ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ባከበሩበት ዕለት፣ በህይወት ዘመናቸው ስላሳለፉት የትግል ጉዞ የሚዳስስ የግል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጀዋር መሐመድ በዛሬው ዕለት ባሰፈሩት ማስታወሻ፣ ገና በለጋ የልጅነት ዕድሜያቸው በኤሌመንተሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በማስተባበር የመጀመሪያውን የተቃውሞ ሰልፍ ካደረጉ 25 ዓመታት ማለፋቸውን አስታውሰዋል። ፖለቲከኛው ይህንን የቆየ የትግል ታሪካቸውን “አገዛዞችን የመጋፈጥ አባዜ” ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ ይህም ስሜት አብሮአቸው የተወለደ እንደሚመስላቸው ገልጸዋል።
በተለይም ጭቆና፣ ብዝበዛ እና መድሎ “አለርጂ” እንደሆኑባቸው የጠቀሱት ጀዋር፣ እነዚህን ድርጊቶች በተመለከቱ ቁጥር ወደ አክቲቪዝም ስራቸው እንደሚመለሱና ይህም ባህሪ እስከ ህይወት ፍጻሜያቸው ድረስ አብሮአቸው እንደሚቆይ ያላቸውን እምነት አጋርተዋል። እድሜያቸው ገፍቶ ጸጉራቸው ቢሸብትም፣ የፍትህ መጓደልን የመቃወም ፍላጎታቸው እንዳልቀነሰም አመልክተዋል።
በመጨረሻም፣ ለልደት በዓላቸው የእንኳን አደረሰህ መልዕክት ያስተላለፉላቸውን ደጋፊዎቻቸውንና ወገኖቻቸውን አመስግነዋል።
