#FastMereja I በዲላ ከተማ የ6 ዓመት ህፃንን አግተው የገንዘብ ክፍያ ሲጠይቁ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት መቀጣታቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ አስታወቀ።
የዲላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዛሬው ውሎው እንዳሻው በቀለ እና ጌቱ ገረመው በተባሉ ተከሳሾች ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል። 1ኛ ተከሳሽ እንዳሻው በቀለ በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲወሰንበት፣ 2ኛ ተከሳሽ ጌቱ ገረመው ደግሞ በ9 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተፈርዶባቸዋል። ግለሰቦቹ ብሩክ ወልደኪዳን የተባለ የ6 ዓመት ህፃንን ከዲላ ከተማ አግተው በመውሰድ በሲዳማ ክልል ውስጥ ደብቀውት እንደነበር በፖሊስ የምርመራ መዝገብ ተመልክቷል።
ተከሳሾቹ ህፃኑን ለመልቀቅ ከቤተሰቦቹ ጋር በገንዘብ ሲደራደሩ የነበረ ቢሆንም፣ የክልሉ ፖሊስ ከአጋር የፀጥታ አካላትና ከህብረተሰቡ ባደረገው የተቀናጀ ክትትል ህፃኑን በሰላም አስጥሎ ለወላጆቹ ማስረከብ ተችሏል። ፖሊስ በወቅቱ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራውን አጣርቶ ለአቃቤ ህግ መላኩንና ፍርድ ቤቱም በቀረበው ማስረጃ መሰረት ጥፋተኝነታቸውን አረጋግጦ ይህንን የፅኑ እስራት ውሳኔ ማሳለፉ ታውቋል።
