banner

በሁለት ማህፀን እና በአንድ ኩላሊት የተወለደችው የ19 ዓመቷ ኬንያዊት አስገራሚ የህይወት ፈተና

​#FastMereja I ሁለት ማህፀን፣ ሁለት የማህፀን በር፣ ሁለት የብልት አካል እና አንድ ኩላሊት ይዛ የተወለደችው የ19 ዓመቷ ኬንያዊት አቢጌል ኬንዲ፣ የገጠማትን አስገራሚና አስቸጋሪ የጤና እክል ይፋ አደረገች። ከተወለደች ጀምሮ ያልታወቀውና ለአጠቃላይ ሐኪሞች እንቆቅልሽ ሆኖ የቆየው ይህ ብርቅዬ የተፈጥሮ እክል፣ የታወቀው ለአቅመ-አዳም ደርሳ የወር አበባ ማየት በጀመረችበት የ14 ዓመት ዕድሜዋ በ2020 ላይ መሆኑን ገልጻለች።

​የወር አበባ ደም ወደ ውጭ መውጣት ባለመቻሉ በሰውነቷ ውስጥ በመከማቸቱ ምክንያት ከፍተኛ የሆድ እብጠትና ህመም ያስከተለባት ሲሆን፣ በመጀመሪያ እርጉዝ ናት ተብላ ተጠርጥራ እንደነበር አስታውሳለች። ይሁን እንጂ በተደረገላት ተጨማሪ ምርመራ ይሄው ያልተለመደ የሰውነት አወቃቀር የተገኘባት ሲሆን፣ ሽንትና ሰገራን በካቴተር (ቱቦ) እና በልዩ የህክምና መሣሪያዎች አማካኝነት ካልሆነ በስተቀር በራሷ ማከናወን እንደማትችል አስታውቃለች። ችግሩን ለመቅረፍና እንደማንኛውም ሴት የወር አበባ እንድታይ ለማድረግ ሰባት ጊዜ የቀዶ ጥገና ሕክምና ቢደረግላትም እስካሁን አልተሳካም።

​ቤተሰቦቿ ለሕክምናዋ ሲሉ ንብረታቸውን በሙሉ የጨረሱ ሲሆን፣ አቢጌል በአሁኑ ወቅት በደረሰባት ከፍተኛ የስነ-ልቦና እና የኢኮኖሚ ጫና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ውስጥ እንዳለች ተናግራለች። ማህበረሰቡ ችግሩን ከተፈጥሮአዊ የጤና እክል ይልቅ እንደ መርገም ወይም መተት እንደሚቆጥረው የገለጸችው ወጣቷ፣ በአሁኑ ወቅት የህክምና እና የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግላት አካል እየፈለገች ትገኛለች።

Leave a Comment