#FastMereja I የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ዛሬ ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ፣ በምሽቱ የአርሰናል ጨዋታ ማጠቃለያ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን የደስታ አገላለጽ ተከትሎ የሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎችን ለመከላከል ሲባል ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ ማንኛውም ሞተር ሳይክል ማሽከርከር መከልከሉን አስታውቋል።
የከተማው ፖሊስ መምሪያ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል እንደገለጸው፣ እገዳው የተጣለው ዛሬ ምሽት 12፡00 ሰዓት ላይ በሚደረገው የኢንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የማጠቃለያ መርሃ ግብር የውድድሩ ሻምፒዮን የሆነው የአርሰናል እግርኳስ ክለብ ደጋፊዎች ደስታቸውን በሚገልጹበት ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የተሽከርካሪ አደጋዎችን ቀድሞ ለመግታት ነው።
ይህ ውሳኔ ያስፈለገው በተለይም ጠጥተው የሚያሽከረክሩ አንዳንድ ሥነ-ምግባር የጎደላቸው ግለሰቦች በማኅበረሰቡ ላይ የአካልና የሕይወት ጉዳት እንዳያደርሱ ለመጠበቅ መሆኑን ፖሊስ በዝርዝር መግለጫው አመልክቷል። በመሆኑም ማንኛውም አሽከርካሪ ጠጥቶ ባለማሽከርከር ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።
የተጣለውን የሰዓትና የትራፊክ ክልከላ ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም አሽከርካሪ ላይ ሕጋዊና ጠንካራ የቅጣት እርምጃ እንደሚወሰድበት መምሪያው አሳስቦ፣ ሕዝቡና አሽከርካሪዎች አስፈላጊውን ቅድመ-ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል። ፖሊስ መልዕክቱን ሲያጠቃልል “ከጠጡ አይንዱ፣ ከነዱ አይጠጡ!” ሲል አስገንዝቧል።
