banner

በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘው ዘመናዊው የላፍቶ ሆስፒታል ተመረቀ

#FastMereja በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ቴክኖሎጂ የተደገፈው እጅግ ዘመናዊው የላፍቶ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል። ግንባታው በ5.4 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውና 17 ዘመናዊ ሕንጻዎችን ያቀፈው ይህ ግዙፍ የሕክምና ማዕከል፣ 500 አልጋዎችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን በተለይም የካንሰር እና የልብ ሕክምናዎችን በላቀ ደረጃ በመስጠት ዜጎች ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ውጭ አገር የሚያደርጉትን ጉዞና የውጭ ምንዛሬ ወጪን ሙሉ በሙሉ ያስቀራል ተብሏል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደገለጹት፣ ይህ የሕክምና ማዕከል በምሥራቅ አፍሪካ ብቸኛና ልዩ የሚያደርጉትን በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የሚደገፉና የ2026 ምርት የሆኑ የረቀቁ የሕክምና መሣሪያዎችን በውስጡ አካትቷል። ከእነዚህም መካከል በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው የሆነው የPET-SCAN የቅድመና ድህረ ካንሰር ምርመራ ማሽን፣ የሂሊየም ትነትን ሙሉ በሙሉ የሚያስቀረው የMRI- 3 Tesla መሣሪያ፣ ልብ አንድ ጊዜ መትታ ሳትጨርስ ሙሉ ምርመራ የሚያከናውነው ፈጣን የCT Scan (640 Slice) ቴክኖሎጂ፣ እና የልብና የአንጎል ደም ሥር ችግሮችን በአጭር ጊዜ ለይቶ የሚያክመው የካዝ ላብ (Cath Lab) ይገኙበታል።

በተጨማሪም የጡት ካንሰርን በቅድሚያ ለመመርመርና የናሙና ምርመራ ለመውሰድ የሚያስችለው 3D ማሞግራፊ፣ ሙሉ በሙሉ ከሰው እጅ ንክኪ ነጻ የሆነውና የሰውን ስህተት የሚያስቀረው የመጀመሪያው የሮቦቲክ ላቦራቶሪ (TLA) ሥርዓት፣ እንዲሁም ዘመናዊ የአልትራሳውንድ እና የዲጂታል ኤክስሬይ ማሽኖች በሆስፒታሉ ውስጥ ተሟልተዋል። ማዕከሉ በሰዓት 80 ሜትር ኩብ ኦክስጂን የማምረት አቅም ያለው የሜዲካል ጋዝ ማምረቻ ፕላንት፣ የራሱ የውኃ ጉድጓድ፣ የፍሳሽ ማጣሪያ ፕላንት እና 18 ዘመናዊ የአስከሬን ማቀዝቀዣዎች ያሉት ሲሆን፣ በሆስፒታሎች የሚያጋጥመውን የኢንፌክሽን ችግር ለመከላከል ሲባልም ግድግዳዎቹና ወለሎቹ ባክቴሪያን ሙሉ በሙሉ በሚከላከል (Anti-bacterial) ቁስ መገንባታቸው ተረጋግጧል። ለፕሮጀክቱ መሳካት ሌት ተቀን ለደገፉ አመራሮችና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።





Leave a Comment