#FastMereja I የቀድሞ የኤር ካናዳ ፓይለት ትክክለኛ የካፒቴንነት ፈቃድ ሳይኖረው ለ17 ዓመታት ያህል በሺዎች የሚቆጠሩ መንገደኞችን በንግድ በረራዎች ሲያጓጉዝ በመቆየቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን የካናዳ ፖሊስ አስታወቀ። ጄፍሪ ዎል የተባለው የ59 ዓመት ፓይለት እ.ኤ.አ ከ2009 ጀምሮ በሀሰተኛ ሰነድ ሲያበር እንደነበር የተደረሰበት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከማጭበርበር ጋር የተያያዙ ሰባት የወንጀል ክሶች ተመስርተውበታል።
ፖሊስ እንዳለው ተከሳሹ ከ1998 ጀምሮ በድርጅቱ ውስጥ በፓይለትነት ሲሰራ የቆየ ቢሆንም፣ በ2009 ወደ ዋና አብራሪነት (ካፒቴን) ካደገበት ጊዜ ጀምሮ ለቦይንግ አውሮፕላኖች የሚፈለገውን ከፍተኛ የበረራ ፈቃድ ሳይኖረው በሀሰተኛ ሰነድ 900 ያህል የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ በረራዎችን አድርጓል። ድርጊቱ ባለፈው ዓመት በተደረገ መደበኛ ግምገማ የሰነድ አለመጣጣም በመታየቱ በምርመራ የተደረሰበት ሲሆን፣ ኤር ካናዳ ግለሰቡን ወዲያውኑ ከስራ ማገዱን ገልጿል።
ድርጅቱ በሰጠው መግለጫ ፓይለቱ መደበኛ የንግድ በረራ ፈቃድ የነበረው በመሆኑ የመንገደኞች ደህንነት ለአደጋ ተጋልጦ እንደማያውቅና ሁሉም አብራሪዎች በየስድስት ወሩ የብቃት ማረጋገጫ ስልጠና እንደሚወስዱ አስታውቋል። እንዲሁም በሌሎች አብራሪዎች ላይ በተደረገ ድንገተኛ ኦዲት ምንም አይነት ተመሳሳይ ችግር እንዳልተገኘ ድርጅቱ ጨምሮ ገልጿል።
