banner

በመጋቢት ኑኑ ገዛኸኝ የተዘጋጀው “የእናትነት ዋጋዉ ስንት ነው?” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ለአንባቢያን በቃ!

#FastMereja I በማኅበረሰቡ ውስጥ የእናቶችን ክብር የሚነኩ አጉል ባህሎችን ለመለወጥና ሥነ-ምግባር የሰፈነበት የመግባቢያ ባህልን ለመገንባት ያለመ “የእናትነት ዋጋዉ ስንት ነው?” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ተመረቀ።

በቤተሰብ እና በቅድመ-ጋብቻ ምክር ላይ ትኩረቱን አድርጎ በሚንቀሳቀሰው “አልባስጥሮስ” የቤተሰብና የሴቶች አገልግሎት ተቋም ዋና ሥራ አስኪያጅ በመጋቢት ኑኑ ገዛኸኝ የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍ፤ ተቋሙ ከተመሰረተበት የአንድ ዓመት ጊዜ ወዲህ ለንባብ ያበቃው ሁለተኛው መጽሐፍ መሆኑ ታዉቋል።

የመጽሐፉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በድምቀት የተከናወነ ሲሆን፣ ከመጽሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ውስጥ የእናቶችን ክብር የሚነኩ፣ የሚያዋርዱ እና የሚያንቋሽሹ አነጋገሮችን ለማስቀረት ለሚደረጉ የሕዝብ ግንዛቤ ማሳደጊያ እና የአድቮኬሲ (የጥብቅና) ሥራዎች የሚውል መሆኑ ተገልጿል።

የተቋሙ ተወካይ በምረቃው ወቅት እንደገለጹት፤ የመጽሐፉ ርዕስ እና የድርጅቱ ስም “አልባስጥሮስ” (ትርጉሙም መልካም እና ውድ ሽቶ የሚቀመጥበት ዕቃ) መሆኑ ከእናቶች ክብርና እንክብካቤ ጋር የተያያዘ መሆኑ ነዉ የተገለፀዉ።

ይህ መፅሀፍ በህብረተሰቡ ዘንድ እናትን የመውደድ ስሜት ቢኖርም፣ በተግባር ግን እናትን የማይመጥኑ አጉል ባህሎችና ስድቦች በመኖራቸው፣ ይህንን የተበላሸ የመግባቢያ ባህል ለመለወጥ መጽሐፉ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል።

ኤልባስጥሮስ የቤተሰብና የሴቶች አገልግሎት ተቋም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከጋብቻ በፊትና በኋላ ባሉ የሕይወት ምዕራፎች ዙሪያ 12 የሚጠጉ ተግባራዊ ሥልጠናዎችን መስጠቱ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት የበርካታ ጥንዶች ትዳር በጥንቃቄ ባለመጀመሩ ምክንያት እየፈረሰ መሆኑን የጠቀሱት ተወካይዋ፣ ተቋማቸው በዋናነት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ያለው ጋብቻ ከመመስረቱ በፊት ባለው “ቅድመ-ጋብቻ” የወጣቶች ዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

በስነ-መለኮት (Theology) እና በሶሺዮሎጂ (Sociology) የትምህርት ዘርፍ በሰለጠኑ ባለሙያዎች የሚመሩት እነዚህ ሥልጠናዎች፤ ተቋሙ መንፈሳዊ ይዘት ያለው ቢሆንም ኦርቶዶክስ፣ እስልምና እና ሌሎችንም እምነቶች ጨምሮ “ሰው ለተባለ ሁሉ” እና ትዳርን ለሚያስብ ማንኛውም ዜጋ ክፍት መሆናቸው ተገልጿል።





Leave a Comment