banner

መንገደኞችን መልካም መንገድ በማለት ውሃ እና ቆሎ የሚሰጡት ሃላባዎች

​#FastMereja | መነሻቸውን ወላይታ ሶዶ አድርገው መድረሻቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ አሽከርካሪዎችና ተጓዦች በሃላባ ዞን ዌራ ዲጆ ወረዳ የክብር አቀባበልና የውሃና ቆሎ ግብዣ እየተደረገላቸው ነው። ተጓዦቹ አዲሱን አማራጭ መንገድ መጠቀም መጀመራቸውን ተከትሎ የአካባቢው ማህበረሰብ የአቀባበል መርሃግብሩን አዘጋጅቷል።

​አሽከርካሪዎችና ተጓዦች ከአዲስ አበባ ወደ ሃላባ፣ ወላይታና አካባቢው ለማቅናት የነበረውን ረጅም መንገድ በማሳጠር በሃላባ ዞን ዌራ ዲጆ ወረዳ በኩል ያለውን የኮረኮንች (ፒስታ) መንገድ መጠቀም ጀምረዋል። ይህ አዲስ መንገድ ምንም እንኳን አስፓልት ባይኖረውም፣ በአሁኑ ወቅት እጅግ አጭር በመሆኑ ተመራጭ ሆኗል። ተጓዦቹ በዚሁ የፒስታ መንገድ አልፈው በስልጤ ዞን ሚቶ ወረዳ ከሚገኘው አስፓልት መንገድ ጋር በመቀላቀል ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ጉዞ በስኬት እያካሄዱ ነው።

​ይህንን አዲስ ጉዞ ምክንያት በማድረግ ሰላም ወዳዱ የሃላባ ማህበረሰብ ለአሽከርካሪዎችና ለተሳፋሪዎች “እንኳን በደህና መጣችሁ፣ ቀጣይ መንገዳችሁ የሰላም ይሁን” በማለት ሞቅ ያለ አቀባበል አድርጎላቸዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች ይህ መንገድ ምንጊዜም ሰላማዊና ምቹ መሆኑን በመግለጽ የውሃና የቆሎ ግብዣ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

​ይህንን በስፍራው የተከናወነውን ህዝባዊ መስተንግዶና አዲስ የጉዞ መረጃ ለ”ፋስት መረጃ” ያደረሰን ናሙስ አባባ ነው።





Leave a Comment