#Fastmereja:-በኢትዮጵያ በሊንክድኢን (LinkedIn) መድረክ ላይ ንቁ ተሳትፎ ላላቸው የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች እና ባለሙያዎች እውቅና ለመስጠት የተቋቋመው “የሊንክድኢን ቼንጅሜከርስ አዋርድስ ኢትዮጵያ (LCAE)” የመጀመሪያውን የሽልማት ስነ-ስርዓት ሊያካሂድ መሆኑን በዛሬዉ እለት በተሰጠ መግለጫ ተገልጿል።
ይህ መርሃ ግብር የፊታችን ሐምሌ 25 ቀን 2018 ዓ.ም (August 1, 2026) በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ቲያትር አዳራሽ በደመቀ ሁኔታ ይካሄዳል።
በጉሩጂ ኤአር ኢትዮጵያ ከዥማ ሚዲያና ፕሮዳክሽን ጋር በመተባበር በተዘጋጀው በዚህ የክብር ምሸት ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የኢንዱስትሪ መሪዎችና የልማት አጋሮች የሚታደሙ ሲሆን፤ በህዝብ ጥቆማ፣ በድምፅ አሰጣጥ እና በባለሙያዎች ጥብቅ ግምገማ ያለፉ ድንቅ እጩዎች ሽልማት ይበረከትላቸዋል።
የጉሩጂ ኤአር ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ያብስራ መካሻ እንደገለጹት፤ ሽልማቱ በሀገሪቱ የሙያ ስነ-ምህዳር ውስጥ የነበረውን ክፍተት ለመሙላትና ይዘታቸው ሌሎችን የሚያነቃቃና ትርጉም ያለው ሙያዊ ውይይት የሚፈጥሩ ሰዎችን ለማበረታታት ያለመ ነው፡፡
ይህ አገር አቀፍ ሽልማት በሳይንስና ቴክኖሎጂ (STEM)፣ በጤና፣ በስራ ፈጠራ፣ በአየር ንብረት እና በማርኬቲንግ ጨምሮ በ6 ዋና ዋና ምድቦች የተከፋፈለ ሲሆን፤ ከዲጂታል መድረክ ባሻገር በተጨባጭ ማህበረሰባዊ ተፅዕኖ የፈጠሩ ባለሙያዎችን ይሸልማል።
የሊንክድኢን ተፅእኖ ፈጣሪዎች ሽልማት ኢትዮጵያ (LCAE) በሀገሪቱ ሙያዊ እና ማህበራዊ መልክዓ-ምድር ላይ በተጨባጭ የሚለካ ተፅዕኖ እያሳደሩ ያሉ ግለሰቦችን እና ድርጅቶችን እውቅና የሚሰጥ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ብሔራዊ፣ ሁለገብ ዘርፍ መድረክ ነው።
#ኹነት




