banner

በምስራቅ ሸዋ በዛሬው ዕለት 20ሺህ የአቮካዶ ችግኝ ተተከለ

​#FastMereja I ግሪን ዌቭ አሊያንስ ከአዋሽ ባንክ እና ከአዋሽ ኢንሹራንስ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዛሬ በምስራቅ ሸዋ ዞን አደዓ ወረዳ ጎዲኖ ጂቱ ወረዳ በታላቅ ሁኔታ ተካሂዷል። በመርሃ ግብሩ ላይ የዞኑ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአዋሽ ባንክና የአዋሽ ኢንሹራንስ ዋና ስራ አስፈጻሚዎች፣ ታዋቂ አርቲስቶችና የአካባቢው ማህበረሰብ በተገኙበት 20 ሺህ የሚደርሱ የአቮካዶ ችግኞች ተተክሏል።

​ይህ በዛሬው ዕለት የተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአካባቢው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና በስነ-ምህዳር ጥበቃ ላይ የጎላ አስተዋጽኦ ለማበርከት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በቦታው ላይ ተገኝተው የአረንጓዴ አሻራቸውን ያኖሩት የነዋሪዎችና የልዑካን ቡድኑ አባላት እንደገለጹት፣ የተተከሉት ችግኞች የምግብ ይዘት ያላቸው የአቮካዶ ዝርያዎች መሆናቸው ማህበረሰቡን በቀጥታ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ታምኖበት የተመረጠ ነው።

​በመርሃ ግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ፣ የአዋሽ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው፣ የአዋሽ ኢንሹራንስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጅባት አለምነህ፣ እንዲሁም የግሪን ዌቭ አሊያንስ መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ አርቲስት ሚካኤል ነጋሳ በጋራ በመሆን ችግኝ ተክለዋል። ከተቋማቱ የስራ ባልደረቦች በተጨማሪ በርካታ ታዋቂ አርቲስቶች እና የማህበራዊ ሚዲያ ተፅኖ ፈጣሪዎች የችግኝ ተከላውን ሂደት በማስተባበርና ህዝቡን በማነቃቃት ረገድ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል።

​ይህን ታላቅ መርሃ ግብር ያስተባበረው ግሪን ዌቭ አሊያንስ ከአረንጓዴ ልማት፣ ከብዝሃ ህይወት እና ስነ ምህዳር ጥበቃ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ በስፋት እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው። ድርጅቱ ላለፉት 5 ተከታታይ ዓመታት የሀገሪቱን የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ በንቃት ሲደግፍ የቆየ ሲሆን፣ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያነቀነቁ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብሮችን በማዘጋጀት እስካሁን ድረስ ከ2.6 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በተሳካ ሁኔታ መትክልና ማጽደቅ የቻለ መሆኑ ይታወቃል።





Leave a Comment