banner

በስዊድን የጎቲያ ካፕ ላይ የተሳተፉ 20 ያህል ኢትዮጵያውያን የቡድን አባላት መጥፋታቸው ተገለጸ

#FastMereja | በስዊድን ጎተንበርግ ከተማ በተካሄደው የጎቲያ ታዳጊዎች ውድድር (Gothia Cup) ላይ ለመሳተፍ የተጓዙ 20 ያህል ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች እና የቡድን መሪዎች ደብዛቸው መጥፋቱን የስዊድን ፖሊስ እና የውድድሩ አዘጋጆች አስታወቁ።

በየዓመቱ በስዊድን በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የታዳጊዎች እግር ኳስ ውድድር ላይ ከተሳተፉ አራት የኢትዮጵያ ቡድኖች መካከል የአንዱ ቡድን አባላት የሆኑት እነዚህ 20 ያህል ግለሰቦች፣ ውድድሩ በተጠናቀቀበት የመጨረሻ ቀን ያረፉበት ትምህርት ቤት ሳይሰናበቱ መውጣታቸው ተሰምቷል። የቡድኑ አባላት እድሜያቸው ከ14 እስከ 17 ዓመት የሆኑ ታዳጊ ተጫዋቾችን እና ከአሰልጣኞች ወይም መሪዎች መካከል የተወሰኑትን ያካተተ መሆኑ ተመልክቷል።

የውድድሩ አዘጋጆች የቡድኑን መጥፋት እንደተረዱ ለአካባቢው ፖሊስ ጥቆማ ያቀረቡ ሲሆን፣ ቡድኑ ወደ ዋና ከተማዋ ስቶክሆልም አቅጣጫ ተጓዥ መሆናቸውን ጠቁመዋል። የስዊድን ፖሊስ ባደረገው ማጣራት እነዚህ ግለሰቦች ወደ ኢትዮጵያ እንዳልተመለሱ ያረጋገጠ ሲሆን፣ ክስተቱ በራሳቸው ፍላጎት የተደረገ መሰወር ወይም ህገ-ወጥ የፍልሰት እንቅስቃሴ እንደሆነ መገመቱን ገልጻል።

የስዊድን የምዕራብ ክልል ፖሊስ የጠፉ ሰዎች ክፍል ተወካይ ኤሊኖር ሃልዲን እንደገለጹት፣ በጉዳዩ ላይ የሰዎች ዝውውር ወይም የወንጀል ድርጊት መኖሩን የሚያሳይ ፍንጭ እስካሁን አልተገኘም። ሆኖም የስዊድን ፖሊስ ከአገሪቱ የኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት፣ ከድንበር ጠባቂዎች እና ከአለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር የቡድኑን አባላት የመፈለግ ሥራ አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል።

Leave a Comment