banner

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ተማሪ በድንገተኛ አደጋ ህይወቷ አለፈ

​#FastMereja I በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ዓመት የህግ ትምህርት ተማሪ የሆነችው ሀብታሟ በቀለ ለእረፍት ወደ ቤተሰቦቿ ከመሄዷ አስቀድሞ በፃድቃኔ ማርያም ቤተክርስቲያን ፀበል በመከታተል ላይ እያለች በተከሰተ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ህይወቷ ማለፉ ተገለጠ። አደጋው የተከሰተው ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ሲሆን፣ ተማሪዋ በአካባቢው በነበረችበት ወቅት ባጋጠመው የመሬት መንሸራተት ህይወቷን ልታጣ ችላለች።

​ተማሪ ሀብታሟ በቀለ በትምህርት ገበታዋ ካስመዘገበችው የላቀ ውጤት ባሻገር በመልካም ስነ-ምግባሯ፣ በታታሪነቷ እና በተግባቢነቷ በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት የነበራት ተማሪ ነበረች። በተለይም በምስለ ችሎት ውድድሮች በምታሳየው የላቀ የህግ ችሎታ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ማህበረሰብ በሚሰጠው የነፃ ህግ እርዳታ አገልግሎት ላይ በንቃት በመሳተፍ የጎላ አስተዋጽኦ ስታበረክት እንደነበር ተገልጻለች።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት በተማሪ ሀብታሟ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጾ፣ ለቤተሰቦቿ፣ ለወዳጅ ዘመዶቿ እና ለመላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ መፅናናትን ተመኝቷል።

Leave a Comment