#FastMereja I ከአጋሮ ከተማ “ጥበብ ብርሃን” የኪነት ቡድን በመነሳት በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ የራሷን አሻራ እያሳረፈች የምትገኘው ድምጻዊት ተዓምር ግዛው፣ ለአራት ዓመታት ስትሰራበት የቆየችውን “በፍቅር” የተሰኘ የመጀመሪያ አልበሟን ነሐሴ 23 ቀን 2018 ዓ.ም ለአድማጮች በይፋ እንደምታበቃ አስታወቀች። አልበሙ በድምጻዊቷ ይፋዊ የዩቲዩብ (YouTube) ቻናል እና በተለያዩ የሙዚቃ ማደመጫ መተግበሪያዎች ላይ የሚለቀቅ ይሆናል።
ይህ 16 የሙዚቃ ሥራዎችን ያቀፈው አልበም የጓይላ (ትግርኛ) እና የፎሌ (ኦሮምኛ) ስልተ-ምቶችን ጨምሮ በኦሮምኛ እና በትግርኛ ቋንቋዎች የተሰሩ ህብረ ብሄራዊ ይዘት ያላቸውን ስራዎች አካቷል። ለአንዱ ሙዚቃ የተሰራው የቪዲዮ ክሊፕ ዝግጅትም ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ ተገልጿል።
በአልበሙ ዝግጅት ላይ በዜማ ደራሲነት አበበ ብርሃኔ፣ እሱባለው ይታየው፣ ምሕረታብ ደስታ፣ አቤል ሙሉጌታ፣ ቢንያምር አሕመድ እና ዳን አድማሱ የተሳተፉ ሲሆን፤ በግጥም ደግሞ ወንድወሰን ይሁብ፣ ዳን አድማሱ እና ጎይትኦም ሃይለማርያም ድርሻቸውን አበርክተዋል። የሙዚቃ ቅንብሩ በሚካኤል ሃይሉ (ሚኪ ጃኖ)፣ ታምሩ አማረ እና ብሩክ አፈወርቅ የተሰራ ሲሆን፣ የ16ቱ ሙዚቃዎች ማስተሪንግ (Mastering) በኪሩቤል ተስፋዬ ተከናውኗል።
ስራውን አስመልክቶ አስተያየቱን የሰጠው የሙዚቃ አቀናባሪው ሚካኤል ሃይሉ (ሚኪ ጃኖ) “ያንጻሉ፣ ያዝናናሉ፣ ያክማሉ ብለን የሰራናቸውን ሙዚቃዎች ለአድማጮች አበርክተናል፤ አስተማሪና አስደሳች ጊዜ አሳልፈን ለዚህ በመብቃታችን አድማጮች ልባዊ አስተያየታቸውን እንዲለግሱ እጠይቃለሁ” ብሏል።
ድምጻዊት ተዓምር ግዛው በበኩሏ ቀኑ በሕይወቷ እጅግ የምትጓጓለት መሆኑን ገልጻ፣ ፈተናዎችን አሳልፈው ለዚህ ላበቋት ባለሙያዎች ምስጋና አቅርባለች። በተጨማሪም ከ”ዮጵ” የተሰጥዖ ውድድር ጀምሮ ላላለያትና ድጋፍ ላደረገላት ድምጻዊ ጸሐይ ዮሐንስ አክብሮቷን በመግለጽ፣ ሁሉም አዳዲስ ባለሙያዎችን የማበረታታት ባህል ሊኖረው እንደሚገባ አሳስባለች። ድምጻዊ ጸሐይ ዮሐንስ አልበሙን በጉጉት እንደሚጠብቀው እና ተዓምር ድንቅ ስራ መስራቷን እንደምትቀጥል እምነቱን የገለጸ ሲሆን፣ የድምጻዊቷ ማኔጀር አቶ ሄኖክ ግዛው በበኩላቸው በአልበሙ ላይ ከፍተኛ ድካምና ጊዜ መዋዕለ ንዋይ ፈሶበት ጥራቱን የጠበቀ ስራ መዘጋጀቱን አረጋግጠዋል።
#ኪነ_ጥበብ




